፫
ትምህርት ቤት በነበራችሁበት ጊዜ ፣ መምህራችሁ ኮስተር ብሎ እና እየደጋገመ ፍጹም ስህተት የሆነ ነገር ሲያስተምራችሁ በአንድ በኩል መምህራችሁን ለማረም እያፈራችሁ ፣ በሌላ በኩል የነገሩ ሐሰትነት እና አስተማሪውን ተከትለው ገደል ሊገቡ የሚችሉ ተማሪዎች መኖራቸው አሳስቧችሁ መላ የጠፋባችሁ ጊዜ የለም ? አንዳንዴ የነገሩ ስህተትነት አይሎባችሁ መምህራችሁን ቀስ ብላችሁ ልታርሙት ስትሞክሩ – ነገሩ ፈጽሞ እንዳልገባችሁ በማሰብ በንቀት ዓይን እየተመለከታችሁ – ይባስ ብላችሁ እሱን ለማረም እንበቃለን ብላችሁ በማሰባችሁ የተሰማውን ብስጭት እና ግርምት በሚያሳብቅ ድምፀት የቀደመውን ስህተቱን ይደግምላችኋል ። እንዲህ ባለ ጊዜ ምንም እንኳን መምህሮቻችሁን “በመርሕ ደረጃ” በእጅጉ የምታከብሩ ተማሪዎች ብትሆኑም – ለዚህኛው መምህራችሁ እና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ለመምህርነትም ሳትፈልጉት ንቀት በውስጣችሁ ታሳድራላችሁ ። እኔም ስለ ዐብዮተኞቻችን እና “ስለ ዐብዮቱ” ጠበቆች ተመሳሳይ ስሜት ያድርብኛል ።
በታላቅ እርግጠኝነት ብርዓቸውን ያነሣሉ ፣ ለረዥም ሰዓታት አፋቸውን ከፍተው ይናገራሉ ። ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ሳይገባቸው ፥ እነሱ ያሉት ተሰምቶ ፣ ይሁን ያሉት ተደርጎ ቢሆን ነገሮች እንዴት የተሻሉ ይሆኑ እንደነበር ይደሰኩራሉ ። ከበቀሉበት የሐሳብ ግንድ ራሳቸውን እንደለዩ ይነግሯችኋል – ነገር ግን በዚያ ግንድ እያለን ልናፈራ ተስፋ ያደረግነውን ያኑ ፍሬ አሁንም እናፈራለን – እንዲያውም ከግንዱ በመነጠላችን ይበልጥ ፍሬያማ እንሆናለን ይሏችኋል ። ልታምኗቸው ትፈልጋላችሁ ፤ ግን ‘ከግንዱ የተለየ ቅርንጫፍ ፍሬ እንዴት ሊያፈራ ይችላል?’ የሚል ግራ መጋባት ውስጥ ትገባላችሁ ። ፈራ ተባ እያላችሁም ትጠይቋቸዋላችሁ ። የጥያቄአችሁ ከንቱነት ያበሳጫቸዋል ፤ የአእምሯችሁ አለመብሰል ያሳዝናቸዋል ። ወላጅ ለሦስት ዓመት ልጁ ዝቅ ብሎ እንደሚያስረዳ ሁሉ ፥ እነሱም ራሳቸውን ወደ እናንተ አጭር ቁመት በማጎንበስ ፥ በድጋሚ ፣ የበለጠ ጊዜ ወስደው ፣ የበለጠ አስፋፍተው ያስረዷችኋል ፤ “ሥርን እና ግንድን ፍሬ ከማፍራት ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም ።”
እውነት ለመናገር እነዚህ ሰዎች በማርክስ እና በሌኒን ጸንተው እንኳን በሆነ የተሻለ ባከበርኋቸው ነበር ። ማርክሳዊነታቸውን ከተዉ በኋላ ግን ፥ እንደማየው ከሆነ ፥ ለብዙዎቹ መሠረታውያን የሚባሉ ነገሮች የሉም ። ስለ ዓለም እና ስለ ህላዌ በጠቅላላው የነበሯቸውን ፥ ሕይወታቸውን እና አላማቸውን የቃኙባቸውን ፥ መሠረታዊ እምነቶቻቸውን እና መረዳቶቻቸውን ከተዉኣቸው በኋላ ፥ ለማሰብ ፣ ለመናገር ፣ ለመጓዝ ሌላ መሠረት ማበጀት እንዳለባቸው አልታያቸውም ። ‘ይህ ነው’ የሚባል ነገር እንዳልተፈጠረ ሁሉ ቀጥለው ያገኙትን ነገር አንሥተው ወደ ፊት ቀጠሉ እንጂ – “ሰሞኑን ከመጣው ጋር ወደ ፊት” እንዲሉ ጓድ ቆምጬ አምባው ። በአሳቢነታቸው እና በተዋሣኢነታቸው እንዳላከብራቸው ፣ ለሐሳቦቻቸውም ክብደት እንዳልሰጣቸው የሚያደርገኝም ይኸው ነው ።
አሁንም እናስባለን ይላሉ ፣ ይናገራሉም ። በምን መሠረትነት እንደሚናገሩ እና እንደሚያስቡ ግን አይነግሩንም ። ይልቁንም – ይህን ጥያቄ አጥብቀው ይሸሹታል ። መሠረታውያን የሆኑትን ነጥቦች ለመመልከት ባለመቻላቸው ወይም ባለመፈለጋቸው – ምንም ረብሕ የሌላቸውን መከራከሪያዎች በማምጣት ተዋሥኦውን ያፍኑታል ። ከማፈኛ መንገዶቻቸው አንዱ በዐብዮቱ ዘመን የተነሡትን ጥያቄዎች እንደ ወረዱ መልሰው በማምጣት እና ትኩረታቸውን ሁነቶች እና ሰዎች ላይ በማድረግ መሠረታዊ ወደ ሆኑት ነገሮች እንዳንመለስ ማድረግ ነው ። ይህን ሲያደርጉ የማርክሳዊነትን መሠረቶችም ሆነ ግቦች ያለ ምንም ጥያቄ “በጓዳ በር” ወደ ተዋሥኦው ይቀላቅሏቸዋል ። ይህ አካሔዳቸው ጥያቄ ካልተነሣበት – ውይይቱ ውስጥ ርእዮት በጭራሽ ጉዳይ አይሆንም ።
ነገር ግን በሆነ አጋጣሚ ፍተሻው በርትቶ ፥ ተዋሥኦው ከሁነቶች እና ከሰዎች አልፎ ወደ ርእዮት ጥያቄ የሔደ እንደሆነ ፥ ሌላ ማፈኛ ተዘጋጅቶለታል ። ይኸውም ማርክሳዊነትንም ሆነ ሌላን ርእዮት ፣ አስተሳሰብ ፣ እንቅስቃሴ ወዘተርፈ ከፍልስፍናዊ መነሻዎቹ ሳይሆን ከግቦቹ አንጻር መመልከት እና መዳኘት ነው ። ወደ ራሳቸው ሚናም ሲመጣ እንቅስቃሴያቸውን እና ድርጊቶቻቸውን ከርእዮታቸው ፣ ከፍልስፍናዊ መነሻዎቻቸው እና በተግባር ከሆኑት ነገሮች አንጻር ከመመልከት ይልቅ የተዋሥኦውን ትኩረት ወደ ነበራቸው ምኞት እና ፍላጎት ይወስዱታል ። ለየትኛውም ርእዮት ቢታደር ፣ የትኛውም ነገር ቢሠራና ቢተገበር “በበጎ ምኞት እና ለጥሩ አላማ” ነው የተደረገው የሚል ክርክር ያመጣሉ ። የእነሱን ሚና በተመለከተ የዚህን ክርክር ታሪካዊ እውነትነት ወደ ፊት የምንፈትሽ ይሆናል ። አሁን ግን ይህ ከግቦች የሚነሣ ክርክር ለምን አመክንዮአዊ እንዳልሆነ እና ፍሬያማ ተዋሥኦ ከማድረግ እያቀበን እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ ።
በጽሑፋችን መግቢያ ላይ እንዳወሳነው ዐብዮተኞቻችን ማርክሳዊነትን ከተዉት ቆይተዋል – ወይም ትተነዋል ካሉ ቆይተዋል ። አንዳንድ ጊዜ ግን የምር መተዋቸውን እንድንጠራጠር የሚያደርጉን ክርክሮች ይገጥሙናል ። ማርክሳዊነት በተለያየ ምክንያት ነቀፋ እና ጥቃት ሲደርስበት – ስለ ቀደመ ባልንጀርነታቸው – ሊከላከሉለት ሲሞክሩ እናያለን ። ምንም እንኳን ቀድሞ ይሉት እንደነበረው “ብቸኛ የመዳን መንገድ” ነው ለማለት ባይደፍሩም ፣ በአጭሩ ሲጠቃለል “ማርክሲዝም በጎ ግቦች ያሉት ርእዮት ስለሆነ ሊኮነን አይገባም ።” በምትል ጋሻ ይከልሉታል ። ችግሩ ፥ ጋሻዋ ከትክክለኛው አቅጣጫ ከተወረወረ ጦር የማታስጥል መሆኗ ነው ። ለምሳሌ ለአቶ አንዳርጋቸው አሰግድ መጽሐፍ መቅድም የጻፉትን የዶክተር ደረጀ አለማየሁን ክርክር እንውሰድ ።
“መጀመሪያ ነገር በተወሰነ የዓለም ክፍል ውስጥ ሰባ ዓመታት ሙሉ በሶሺያሊዝም ስም ብዙ ወንጀሎች ስለተፈጸሙ ፣ አገራችንም በሶሺያሊስት ነኝ ባዩ ደርግ ሥር ስለማቀቀች ፣ በየትኛውም መንገድ ከዚህ ርእዮተ ዓለም ጋር የተያያዘ ዐብዮት ምሬትና ጥላቻን መቀስቀሱ ስለማይቀር ሚዛናዊ ፍርድ ለማግኘት ያስቸግረዋል ። ሁለተኛ ደግሞ ፣ (እንጀራ) አባቱ ሶቭየት ኅብረት ከፈረሰ ወዲህ ከናካቴውም ‘ሶሺያሊዝም አለቀ ፣ ደቀቀ’ ስለተባለ ፣ ይህ ዐብዮት ላነሣቸው ፣ ሊመልሳቸው ለሞከረውና ላቃተው ጥያቄዎች ሁሉ ‘ሶሺያሊዝም ዋጋ የለውም ፣ እንደማይሠራ ተረጋግጧል’ የሚል ውይይት አፋኝ መልስ ተዘጋጅቶላቸዋል ።
“ሃይማኖት እንደገና የተስፋፋበት ዘመን ስለሆነ የሃይማኖት ምሳሌ ልውሰድና ፣ ሶሺያሊዝም የተባለው ሃይማኖት ምእመናን ብቻ ሳይሆን ዲያቆ(ናት) ለነበርነው ለእንደኔ ዓይነቱ ጥያቄው እንዲህ ግልጽ ፣ መልሱም እንዲህ ቀላል አይደለም ። በበኩሌ በዚህ ርእዮተ ዓለም ስም ለተፈጸሙ ወንጀሎች ርእዮተ ዓለሙን ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ ዛሬም ይከብደኛል ። ከሃይማኖት ሳንወጣ ከአሠርቱ ቃላተ ኦሪት ‘አትግደል’ የሚለውን ትእዛዝ እንውሰድ ። (አንዳንዴም) በሃይማኖት ስም አማኞች ሲጋደሉ ኖረዋል ። መግደል ግን በአጠቃላይ ሰብአዊነትን ብቻ ሳይሆን የዚህ ሃይማኖትንም ድንጋጌ ነው የሚጥሰው ። አማኙና ሃይማኖቱ ተነጣጥለው አይታዩም ካልተባለ በስተቀር ወንጀሉን ሃይማኖት ላይ ማላከክ ይቻላል ? መግደልን ስላላገደ ሃይማኖት ዋጋ የለውም ማለት ግን ይቻላል ።
“በሌላ በኩል ደግሞ ፣ ሶሺያሊዝም አይሠራም ስለሚባለው የፖለቲካ አላማዎች ሁሉ ያለን ሁኔታ ለማሻሻል የሚነደፉ የወደፊት ውጥኖች እስከሆኑ ድረስ ገና በተግባር ስላልታዩ የግድ ሕልማዊ (ዩቶፕያን) ናቸው ። ሶሺያሊዝም በዚህ ጎኑ ከሌሎች የፖለቲካ አላማዎች አይለይም ።”[1]
ዶክተሩ ሁለት መሠረታዊ ስሕተቶችን ሠርተዋል ። የመጀመሪያው ስሕተታቸው ማርክሳዊነትንም ሆነ ክርስትናን ለማምጣት ካለሟቸው ግቦች አንጻር ለመመዘን እና “ዋጋ” ለመስጠት ማሰባቸው ነው ። በሌላ አነጋገር ፥ “ተፈላጊውን” ነገር ዒላማ እስካደረገ ድረስ አንድ ርእዮት የመነሻዎቹ እውነትነት ችግር የለውም ፤ ዞሮ ዞሮ ዶክተሩ ከርእዮቱ መነሻ ይልቅ ያሳሰባቸው እና ከወቀሳ ያድነዋል ብለው ያሰቡት “በጎ ግቦች” ያሉት መሆኑ ነው ። ከዚህ አካሔዳቸው አንጻር ዶክተር አለማየሁ በፍጹም እውነት እና የሞራል ሕግ መኖር የማያምኑ (relativist) እና አብዛኛውን ሰው እስካስደሰተ ድረስ ትክክል ነው ባይ (utilitarian) ይመስላሉ ።
ምክንያቱም የፍጹም እውነት መኖር እና አስፈላጊነት እስከታመነ ድረስ ማርክሳዊነት (ወይም ማንኛውም ሐሳብ እና ርእዮት) ለማምጣት ካለመው ወይም ካመጣው ውጤት አንጻር አይደለም በመጀመሪያ ሊመዘን የሚገባው – ስለ ዓለም ያለው መረዳት ትክክል ከመሆኑ አንጻር እንጂ ። ዶክተር አለማየሁም ተስፋ እንደማደርገው ፍጹም እውነት እና የሞራል ሕግ መኖራቸውን ቢያንስ “በመርሕ ደረጃ” የሚቀበሉ ከሆነ በዚህ ክርክራቸው ገና ከመነሻው ‘ሸቃባ’ ሚዛን ይዘው የተነሡ መሆኑን ላረዳቸው እወዳለሁ ። እንዲያውም ሙከራቸው ከተዛባ ሚዛን ትክክለኛ ልኬት ከመጠበቅ ይልቅ ክብደትን በሜትር ለመለካት መሞከርን ይመስላል ።
ማርክሳዊነት አንድን ችግር ለመፍታት የተዘየደ መላ አይደለም – የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዳ ርእዮት ነው እንጂ ። ከላይ እንዳየነው ማርክስም ሆነ ኤንግልስ ወይም ስታሊን – ማርክሳዊነትን የሚመለከቱት ነገሮችን “እንደሆኑ አድርጎ” የሚገልጽ አድርገው ነው እንጂ አንዳች ተምኔትን አሳድዶ ለመያዝ የሚጠቅም መሣሪያ አድርገው አይደለም ። ተወደደም ተጠላም – “ሰፊው የወዛደር መደብ በመጨረሻ ማሸነፉ አይቀርም” – ፀሐይ መውጣቱ ፣ ወተት መርጋቱ እንደማይቀር ሁሉ ። “የሶሺያሊዝም ዲያቆን” የነበሩ እንደመሆናቸው ይህን አያጡትም መቼም ።
ስለዚህ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ “ዓለም በውኑ ማርክሳዊነት ናት እንደሚላት ናትን ?” የሚል ነው ። በሌላ አነጋገር – የማርክሳዊነት ፍልስፍናዊ መሠረቶች ትክክለኝነት ነው መጠየቅ ያለበት ። ለምሳሌ “ሁሉም ነገር ቁስ አካል ነው ?” – ካልሆነ ማርክሳዊነት ምንም ቢያልም ፣ ምንንም አላማ ቢያደርግ ዋጋ የለውም ።
ዶክተሩ ግን ሐሳቦችን እና ርእዮቶችን ከትክክለኛነታቸው ይልቅ ከግቦቻቸው መልካምነት ወይም “ተፈላጊውን ውጤት” ከማስገኘታቸው አንጻር ለመመዘን ሲነሱ ጥቅመኛ (utilitarian) እየሆንሁ ወይም የፍጹም እውነታን መኖር እየካድሁ ነው ብለው የሚያስቡ አይመስለኝም ። በእሳቸው ቤት “መልካም” የተባሉት ግቦች የታወቁ ፣ የተረዱ ፣ የማይጠየቁ ናቸው ። ማስረጃ ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን በርሳቸው የሚያስረዱ ፣ ምንም ላይ መመሥረት የማያስፈልጋቸው በራሳቸው የሚቆሙ የእውነት መሠረቶች ናቸው ። ሁለተኛውና ዋነኛው ስሕተታቸውም ያለው እዚህ ጋ ነው ።
ይህን ለማብራራት ራሳቸው ከሃይማኖት ጋር የሠሩትን ንጽጽር ልጠቀም ። እውነት ነው ፥ አንድ ክርስቲያን በመግደሉ ኃጢአት ይሠራል ። ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህን ኃጢአት ፈጽመውታል ፤ ይፈጽሙትማል ። ስለዚህ ይላሉ ዶክተር ፥ “መግደልን ስላላገደ ሃይማኖት ዋጋ የለውም ማለት ይቻላል ።” በእሳቸው መረዳት ክርስትና ሰዎች እንዳይገድሉ ፣ እንዳይሰርቁ ፥ ሌሎችን “ክፉ” ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ “ለማገድ” “የተፈጠረ” ነው ። ነገር ግን ከላይ እንዳልነው ይህ መረዳታቸው አንጻራዊነት እና ጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ ስሑት መረዳት ነው ። ክርስትና ምንም ነገር “ለማገድ” “የመጣ” አስተምህሮ አይደለም ። ክርስቲያኖች ሁሉ በኃጢአት ቢዋጡም የክስትናን ዋጋ አልባነት አያሳይም – ምክንያቱም ክርስትና የተገለጠ እውነት እንጂ ወደ አንዳች ጥቅምን ለማስገኘት ወይም አንዳች ችግርን ለመፍታት የተፈለሰፈ ዘዴ አይደለም ። ክርስትና ብቻ ሳይሆን ማርክሳዊነትም ከላይ እንዳልሁት በዚህ መልኩ መታየትን አይሻም ።
ዶክተር አለማየሁ ክርስትና “መግደልን ካላስቀረ . . .” ሲሉ – መግደል መቅረት ያለበት ነገር መሆኑ ያለ ነጋሪ የታወቀ ነው እያሉ ነው ። የክርስትና ሥራ – እንደ እሳቸው ከሆነ – ይህን የታወቀ “ክፉ ተግባር” ማስቀረት መቻል ነው ። ነገር ግን የመግደል ክፋት የታወቀ ነገር ነው የሚል መነሻቸው እውነት አይደለም ። እውነት አለመሆኑንም ለማሳወቅ የእሳቸውና የወዳጆቻቸው ታሪክ በቂ ነው ። ማርክሳውያን በነበሩበት ዘመን – ‘መግደል መጥፎ ነው ፣ መቅረት አለበት ።’ የሚል ሐሳብ አልነበራቸውም ። እንዲያውም (አለፍ ብለን እንደምናየው) መግደል የተወደደ ነገር ነበር – ተገዳዩ “አድኃሪና በዝባዥ” እስከሆነ ድረስ ።
የክርስትና ሚና መግደል መጥፎ መሆኑን መንገር ነው ማለቴ አይደለም ። ይልቁንም መግደል መጥፎ የሆነው ክርስትና እውነት ስለሆነ ነው ። ክርስትና እውነት ካልሆነ – ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ካልተፈጠረ – ማርክሳዊነት እንደሚለው ሁሉም ነገር “ቁስ አካል ብቻ” ከሆነ – አንድን ውሻ ፣ አንድን በግ ፣ ወይም አንዲትን ቁጫጭ በመግደል ወይም አንድን ድንጋይ በመፍለጥ እና አንድን ሰው በመግደል መካከል ምን ልዩነት ይኖራል ? የሰውን ሕይወት ከሌላው “ቁስ አካል” የተለየ እና ከፍ ያለ ዋጋ ያለው የሚያደርገው ምንድነው ? በተቃራኒው ማርክሳዊነት ትክክል ከሆነ – ፀረ ዐብዮተኞችን መግደል የጽድቅ ተግባር (righteous deed) መሆኑ ነው ። (በእርግጥ በሌላ በኩል – ማርክሳዊነት deterministic ስለሆነ ማንንም በሥራው ለመንቀፍም ሆነ ለማመስገን የማይቻልበት ዓለም ነው – ግን ይህን ቅራኔ በኋላ እንመጣበታለን) ።
ስለዚህ መግደል መጥፎ እና መቅረት ያለበት መሆኑ ያለ ምንም ማስረጃ “የታወቀ እና የተረዳ” ነገር አይደለም ። ፈጽሞ ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሁሉም “ተፈላጊ” ግቦች ጽኑዕ እና እውነተኛ በሆኑ ፍልስፍናዊ መነሻዎች ካልተደገፉ በስተቀር ትርጉማቸውም ሆነ መፈለግ የሚገባቸው መሆኑ አይታወቅም ። መፈለጋቸውም በራሱ መፈለግ ያለባቸው መሆኑን አያሳይም ። ለዚህም ነው አንድ ርእዮት በግቦቹ ሊመዘን የማይችለው ።
“እኩልነት” ስንል ምን ማለታችን ነው ? በሰዎች መካከል ብቻ ነው ወይስ በሰዎች እና በእንስሶችም መካከል ? ሰዎች እውነትም በመጠን እንጂ በዓይነት ከእንስሳት የማይለዩ “ማኅበራዊ እንስሶች” ከሆኑ ከሌሎች እንስሶች በላይ የሚሆኑት ለምንድነው ? ማገናዘብ በመቻላቸው የሚል ሰው ካለ – በቅድሚያ ማገናዘብ ለምን ከፍ ያለ ቦታ እንደሚያሰጥ ግልጽ አይደለም ። ግን ያሰጣል ከተባለ – ያነሰ የማገናዘብ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከእንስሳት እኩል መቁጠር እንችላላለን ማለት ነው ? “ፍትሕ” ስንልስ ምን ማለታችን ነው ? በቀል ፍትሐዊ ነው ? ምሕረት ማድረግስ ፍትሕን ማጓደል አይሆንም ? ዲሞክራሲያዊ በሆነ ውሳኔ ሕዝብ – ዘጠና በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ቀሪውን አሥር በመቶ ለማጥፋት ቢወስን ችግር አለው ? እርግጥ ነው ሁሉም ሰው “የመኖር መብት” አለው ሊባል ይችላል – ግን አባቶቻችን ማርክስ እና ኤንግልስ እንዳስተማሩን ሁሉም ነገር “ቁስ አካል ብቻ” ከሆነ ሰውን ከሌላው ሁሉ ቁስ አካል ለይቼ ለማየት ምን ምክንያት ይኖረኛል? የተባለውንስ “መብት” ለሰው ማን ሰጠው ? የታወቀ መብት ሰጪ ከሌለ ደግሞ ይህ “መብት” የሰዎች ፈጠራ እንጂ እውነት ስላልሆነ መግደል ለምን ችግር ይሆናል ? ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ደካሞች ቢጠፉ ምንድነው ችግሩ ? ከራሴ ይልቅ የማኅበረ ሰብእን ወይም “የሰብአዊነትን” “ጥቅሞች” ማስቀደም እንዳለብኝ እሰማለሁ ። ግን ለምን ? የራሴ ደስታም ሆነ ሕመም የሚሰማኝ ለራሴ ሆኖ ሳለ በእኔ መቃብር ላይ የሌሎች ደስታ የሚገነባበት ምክንያት ምንድነው ? የሌሎችን ጥቅም ለማስቀደም ከወሰንሁ ደግሞ ለምን በቤተሰቤ ፣ በሀገሬ ወይም በሰብአዊነት እታጠራለሁ ? እንስሳትን እና ዕፅዋትን ከጥፋት ለማዳን ሰዎችን ብገድልስ ? እንዲያውም አሁን አሁን እንደሚባለው የሰው ልጅ ምድሪቱን ለጥፋት እየጋበዘ ከሆነ – የሰውን ልጅ በማጥፋት ምድሪቱን ከጥፋት መታደግ ጽድቅ አይሆንም ? ዞሮ ዞሮ መኖር ከአለመኖር መሻሉ ግልጽ አይደለም – ምንም እንኳን በደመ ነፍስ ቢፍጨረጨሩም – ከሕይወት ከባድነት እና ትርጉም አልባነት አንጻር ሲታሰብ ግን ለሰዎች ከመኖራቸው ሞታቸው አይሻላቸውም ? እንደዚህ ባሉትና በሌሎችም ብዙ መንገዶች ምንነታቸው ፣ ተፈላጊነታቸው እና አስፈላጊነታቸው “አይጠየቁም” የሚባሉት ዕሴቶች እና ግቦች መጠየቅ ይችላሉ ፤ ይጠየቁማል ። ጽኑዕ እና ርቱዕ ከሆነ መሠረት ሌላ ከዚህ ወጀብ ሊታደጋቸው የሚችል የለም ።
ዶክተር ዓለማየሁ የሠሩት ሌላው ትልቅ ስሕተት ደግሞ የተዛባ ንጽጽር ማድረጋቸው ነው ። ምንም እንኳን ከውጤት ተነሥቶ የርእዮቱን “ዋጋ” መገምገም ትክክል ባይሆንም ግን ለአንድ አፍታ ይህን ለማድረግ እንፍቀድ ። ክርስትናን እሳቸው “ዋጋ የለውም” ያሉት – እሱ የከለከለውን ነገር ሰዎችን ከማድረግ አላገደም ብለው ነው ። ሶሺያሊዝም ላይ ግን የቀረበው ክስ ይህ አይደለም ። የሶሺያሊዝም ትእዛዛት በመከበራቸው ብዙ ጥፋት ደረሰ ነው እየተባለ ያለው ። ማርክሳዊነት – “አትግደል” አይልም – ይልቁንም “Force is the midwife of every old society pregnant with a new one.” ነው የሚለን (Stalin, p. 36) ። በማኒፌስቶአቸው ማርክስ እና ኤንግልስ ፉርዬ ፣ ኦውን እና ሴንት ሳይመን የተባሉትን ቀደምት ሶሻሊስቶች የሚተቹበት አንዱ ነጥብ “ፖለቲካዊ እና ዐብዮታዊ እንቅስቃሴዎችን ይቃወማሉ ፤ በምትኩም በሰላማዊ መንገድ ፣ እና ማኅበራዊ ሙከራዎች በማድረግ ወደ ሶሻሊዝም ለመድረስ ያልማሉ ።” የሚል ነው[2] ። በሰላማዊ መንገድ ወደዚህ ግብ ለመድረስ መሞከር ግን የማርክሳዊነት መሠረት የሆነውን “ቅራኔያዊ ዘይቤ” ይፃረራል ፤ በመሆኑም ትክክል አይደለም ። በመደቦች መካከል ባለው ትግል ኃይል እና መጠፋፋት መኖሩ ግድ ነው ።
ከዚህ ማርክሳዊ መርሕ በመነሣት ነበር በዐብዮተኞቹ የተወደደ የነበረው ጸሐፊ ፍራንዝ ፋነን ከ‘violence’ (ኃይል ፣ ነውጥ ፣ ደም ማፍሰስ) ስለሚገኘው መንፃት እና ማኅበራዊ ዐብዮት ይሳካ ዘንድ ፣ ተጨቋኞች ለራሳቸው ያላቸው ክብር ይመለስ ዘንድ ይህ “መንፃት” መከናወኑ የግድ መሆኑን የተናገረው[3] ። ለማርክስ እና ለፋነን የታመኑት የኛ ዐብዮተኞችም እንዲሁ ጭቆና እንዲጠፋ የግድ የትጥቅ ትግል መኖር አለበት ባዮች ነበሩ ። ዋለልኝ “እውነተኛ የእኩልነት ሀገር ለመገንባት ብቸኛው መንገድ የኃይል እና የትጥቅ ትግል ነው ።” ሲል የገዛ አቋሙን እየገለጠ አልነበረም ፤ ለማርክሳዊነቱ እየታመነ እንጂ (Quest p. 201) ። “በዐብዮቱ” ሒደት ያየነው መገዳደል እና መጠፋፋት በራሱ በማርክሳዊነት የተበረታታ መሆኑ አያሻማም ።
ኅዳር 14 ፣ 1967 – 60ዎቹ በተገደሉ ማግሥት ዐብዮተኞቻችን የወሰዱት አቋም ይህን መታመናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ። በዚያ ቀን ኢሕአፓ እና መኢሶን ኀዘናቸውን የገለጡት – ከ60ዎቹ መካከል 6 ወይም 7 ዐብዮተኞች ተቀላቅለው በመገደላቸው ነበር ። ምንም እንኳን ኢሕአፓ እና መኢሶን አብሮ ለመሥራት የማያስችሏቸው እና በመጨረሻም እስከ መጠፋፋት ያደረሷቸው ልዩነቶች በመካከላቸው ቢኖሩም በዚህ ጉዳይ ግን ሁለቱ ወገኖች ተነጋግረው ያደረጉት ያህል አመክንዮአቸውም ሆነ አስተያየታቸው ፣ ቋንቋቸውም ጭምር አንድ ዓይነት ነበር ። መኢሶን በዚያ ሁነት ማግስት የሰጠው መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል ።
“ኅዳር 14 ሳይታሰብ ፣ ሳይጠረጠር ስድሳ ሰዎች በድንገት ተረሽነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ዓለም በቃኝ አጥር ስር ተቀበሩ ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ለ30 ዓመታት ያህል ፣ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ተንሰራፍተው በመቀመጥ ፣ ሰፊውን ሠርቶ አደር ሕዝብ ሥጋውን በልተው ደሙን ጠጥተው በአጥንቱ ያስቀሩት የኃይለ ሥላሴ ፍጡሮች ናቸው ። ሌሎቹ ደግሞ የነበረውን የጭቆና መንግሥት በመቋቋም ፣ በማንበርከክና በመጣል ከሰፊው ሕዝብ ጋር ተሰልፈው የነበሩ ናቸው ።
“(እነዚህ) ለብዙ ወራት እሥር ቤት ቆይተው ፤ ሕግ ወጥቶ ፤ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ፤ ፍርዳችሁን ትቀበላላችሁ በመባል ሲጠባበቁ ቆይተው (አሁን) በድንገት ያለ ምንም ምክንያት በጥይት ተደበደቡ ።
“ለመሆኑ የርሸናው ውሳኔ የተወሰደው ፣ የሚረሸኑትስ ምርጫ የተከናወነው በእንዴት ያለ መንገድ ይሆን ? ደግሞስ የሰፊው ሕዝብ ወገን የሆኑት ታጋዮችን ከበዝባዦች ጋር መረሸን ከሥልጣን ጥማት የመነጨ እብደት እንጂ ሌላ ምንን ያሳያል ?
“በነሻምበል በላይ ፀጋየ ፣ ሻምበል ወልደ ዮሐንስ ዘርጋው ፣ በነምክትል አሥር አለቃ ተክሌ ኃይሌ እኛ በሌሎችም የሰፊው ሕዝብ ወገኖች ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ ፣ ሰፊው ሕዝብ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን እና ሻምበል ሲሳይ ሀብቴን ወደፊት ይፋረዳቸዋል ።”[4]
ኢሕአፓም ዲሞክራሲያ በተባለው ልሳኑ ያስተጋባው ሐሳብ ተመሳሳይ ነበር ።
“ወደ ትናንት ማታው ግድያ ስንመለከት ደግሞ በዚሁ ባወጡት ፋሺስታዊ አዋጅ ሥርዓት እንኳን ሊመሩ አለመቻላቸውንና ተራማጆችን ለማጥፋት የማይፈጥሩት ምክንያት እንደሌለ በገሃድ እንመለከታለን ።
“ጅብን ሲወጉ በአህያ ተጠግቶ እንደተባለው ፣ ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና ድሮ ከፈረደባቸው ፣ ገና ድሮ በልቡ ከሰቀላቸው መሳፍንት እና መኳንንት ጋር እነማን /“በሰሎሞናዊ ጥበብ”/ ተሰባጥረው ተገደሉ ?
“—– እነዚያ በየካቲቱ እንቅስቃሴ የትግሉ ቀደምት የነበሩት —– እነዚያ ድምፃቸው ከሠፊው ሕዝብ ድምፅ ጋር በማስተባበር ፣ የሕዝብ መሠረታውያን መብቶች እንዲከበሩ የጠየቁት —– የባዕዳንን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ የተቃወሙት —– አምባገነንነትን በመቃወም ፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም የጠየቁት፣
በጥቅም ያልጎደፉ ፣ በሥልጣን ያልተመረዙ ፣ አፍላ ወጣት ሀገር ወዳዶች ፣
- ሻምበል በላይ ጸጋዬ /ከአርሚ ኤቪዬሽን/
- ሻምበል ደምሴ ሽፈራው /ክቡር ዘበኛ/
- ሻምበል ወልደ ዮሐንስ ዘርጋው /መሐንዲስ/
- ተራ ወታደር በቀለ ወልደ ጊዮርጊስ /መሐንዲስ/
- የመቶ አለቃ ተስፋዬ ተክሌ
- ጁኒየር ኤክ ማን ዮሐንስ ፍትዊ
የመሳፍንቱ ሥርዓት ፣ እንዲሁም ማንኛውም የብዝበዛ ሥርዓት ፣ በማያዳግም ሁኔታ እንዲደመሰስ ፣ እስካልተፈጸመ ድረስ ደማቸው ጥሪውን አያቆምም ።”[5]
እነዚህ መግለጫዎች ማርክሳዊነት የተማሪዎቹን አእምሮ እንዴት እንደቀረጸው በደንብ የሚያሳዩ ይመስለኛል ። ምንም እንኳን ደርግ 60ዎቹን ሲገድል ያለ ሕግ ቢሆንም – ኢሕአፓ እና መኢሶን ግን ደርግን የተቹት ግን ያለ ሕግ ተራማጆችን በመግደሉ ነው እንጂ ከተጠቀሱት ውጪ የሞቱት ሰዎች በሙሉ ያለ ሕግ መሞታቸው አላሳዘናቸውም ። እንዲያውም የእነሱ ሞት የተጠቀሱትን ሰዎች ለመግደል እንደ ሰበብ ጥቅም መዋሉ እንጂ ክፋቱ ፥ ሰዎቹ “ሰፊውን ሠርቶ አደር ሕዝብ ሥጋውን በልተው ደሙን ጠጥተው በአጥንቱ ያስቀሩ” እንደ መሆናቸው ፥ “ሰፊው ሕዝብም ቀድሞ በልቡ ስለፈረደባቸው እና ስለሠቀላቸው” (እና ሰፊው ሕዝብ ስለማይሳሳት) ግድያቸው ትክክል እንደሆነ ያምናሉ ። ዶክተሩ አቻ ያልሆነ ንጽጽር ነው ለመሥራት የሞከሩት ። ከውጤቱ አንጻር ማርክሳዊነት የተጠላው ባለመከበሩ ሳይሆን በተከበረበት ቦታ እና ዘመን ባመጣው ውጤት ነው ። በውድቀቱ አይደለም በስኬቱ ነው ።
ነገር ግን አሁንም ከዋናው ነጥብ መናጠብን አንፈቅድም ። በዶክተሩ ምሳሌ እና የተዛባ አመክንዮ ውስጥ ልብ ልንለው የሚገባን አካሔዳቸው የአንድን ርእዮት “ዋጋ” እውነተኛ ከመሆኑ አንጻር ሳይሆን ከሚያመጣው – ወይም ለማምጣት ከሚያልመው ውጤት አንጻር ለመለካት የሚሞክሩ ፤ እንዲሁም “ተፈላጊዎቹ” ውጤቶች የታወቁ እንደሆኑ የሚያስቡ መሆናቸው ነው ።
ፕሮፌሰር ባሕሩም እንዲሁ ማርክሳዊነትን በአንድ እጃቸው እየገፉ በሌላ ክንዳቸው ያቅፉታል ።
“Communism may be dead, but capitalism is still plagued with periodic crises – evidence, if any were needed, that it is not the perfect system its advocates claim it to be. Leninism may be démodé. But Marxism as an analytical tool continues to have relevance. Many student activists who participated in the movements of of the 1960s and 1970s owe to them some of the enduring features of their personalities, such as gender sensitivity, multiculturalism and viewing authority with a salutary dose of irreverence.”[6]
ልክ ዶክተሩ ላይ እንዳየነው ሁሉ ፕሮፌሰር ባሕሩም ርእዮትን ቋሚ እና ዘላቂ እውነት ሳይሆን እንደ ፋሽን በየጊዜው የሚለዋወጥ ነገር አድርገው ማየታቸውን ልብ በሉልኝ ። ዳግመኛም ማርክሳዊነትን እውነት ከመሆኑ ወይም ካለመሆኑ አንጻር ሳይሆን “ከጠቃሚነቱ እና ከግቦቹ በጎነት” አንጻር ማየታቸውንም እንዲሁ ። ዕሴቶች ያለ ፍልስፍናዊ መሠረት ይቆማሉ ብለው ማሰባቸውም የሚታይ ነው ። እነዚህን ነጥቦች ከላይ ስላነሣኋቸው አልመለስባቸው ። ነገር ግን ማርክሳዊነት “እንደ ትንተና መሣሪያ” ጠቃሚ ነው ማለታቸውን እንተች ።
እውነት ነው ፣ አሁንም ቢሆን ማርክሳዊነት በዘመናዊው ትምህርት ውስጥ በእጅጉ ተጽዕኖ አሳዳሪ ሆኖ ይገኛል ። በ እያንዳንዱ “የማኅበራዊ ሳይንስ” ዘርፍ ውስጥ ማርክሳዊነት ወይ የአባትነት ሚና አለው ፤ አሊያም የክብር ወንበር ክቡራን መካከል አንዱ ነው ። ይህ መሆኑ ግን የማርክሳዊነትን ትክክለኝነት ወይም “ጥቅም” የሚያሳይ አይደለም ፤ ዘመናዊው ትምህርት በጠቅላላው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መሠረታዊ እሳቤዎቹን ከማርክሳዊነት ጋር እንደሚጋራ ያሳያል እንጂ ።
ጆን ማርካኪስ በዐብዮቱ ዋዜማ የጻፈውን “Ethiopia; Anatomy of a Traditional Polity” የተሰኘ መጽሐፍ ምሳሌ እናድርገው ።መጽሐፉ ፕሮፌሰር ባሕሩ እንደሚሉት “መደባዊ ትንታኔን” (class analysis) በመጠቀም የተጻፈ ነው ። መጽሐፉ የደንበኛ ጥናትና ምርምር ውጤት ነው ። ነገር ግን እኔ ሳነብበው በአንድ ነገር ተቸግሬ ነበር ። በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ታሪካዊ ሐቆቹ በማይገባ እና በተጣመመ መንገድ ተደራጅተው እና ተተርጉመው – አንዳንድ ሐቆች ከሚገባው በላይ ዋጋ ተሰጥቷቸው – ሌሎች ደግሞ የሚገባቸው ቦታ ተነፍጓቸው እመለከታለሁ ። ነገሮችን አጥብቦ የሚመለከትበት መንገድ እና ከታሪካዊ እውነታዎች ተነሥቶ የሚደርስበት ስሑት ድምዳሜ ያበሳጨኛል ። ነገር ግን ከትንተናዎቹ እና ከድምዳሜዎቹ ጋር ሙግት መግጠም ፍሬ ቢስ መሆኑ ግልጽ ነበር ። የድምዳሜዎቹ ልዩነት የተፈጠረው መነሻዎቹ ላይ ካለው ልዩነት የተነሣ ነውና ። ማርካኪስ ራሱ “መደብን” እንደ “ትንተና መሣሪያ” መጠቀሙ አሳሳቢ እንደሆነ “በዚህ ዓውድ” የነገሮችን ሙሉ ስዕል ላይሰጥ እንደሚችልም ይገነዘባል ።
“The concept of class is used in this study as a tool of analysis, not as a philosophical postulate even though it is perceived in its classical form which integrates privilege, power and status in a single hierarchy. Its application to an African society that is still largely traditional is, admittedly, not in accordance with conventional practice. Social scientists generally maintain that classes have not yet developed among traditional African societies, and cite the kinship system of social organization, communalism of land holding and general lack of surplus as the inhibiting factors.”[7]
ማርካኪስ “እንደ ትንተና መሣሪያ” እንጂ እንደ ፍልስፍናዊ ፅንሰ ሐሳብ አልተጠቀምሁትም ማለቱ ለምን ትርጉም እንደማይሰጥ ከመመልከታችን በፊት አንድ ነገር ልብ እንበል ። “መደብን” “እንደ ትንተና መሣሪያ” መጠቀም በአፍሪካ ዓውድ ተገቢ አይደለም ተብሎ የተሰጠው ምክንያት በራሱ ማርክሳዊ ነው ። ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች የአፍሪካ ማኅበራተ ሰብእ ውስጥ “መደብ” ገና አልተፈጠሩም ወይም አልዳበሩም ሲሉ – ወደ ፊት ግን ይፈጠራሉ ፤ ይዳብራሉም ። ያኔ ይህን ፅንሰ ሐሳብ መጠቀም ተገቢ ይሆናል እያሉ ነው ። ስለዚህ ከቁሳዊ ሁኔታ መለዋወጥ የተነሣ የማኅበረሰቡ መዋቅር በቅራኔአዊ ሒደት “እያደገ” መሔዱ አይቀርም የሚለውን ባለፈው ክፍል ያየነውን “ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊ” መነሻ ሳይንቲስቶቹም ሆነ ማርካኪስ ራሱ ተቀብለውት እናገኛቸዋለን ። ይህ ማርክሳዊነት ዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንደ ሕዋ ከመንሠራፋቱ የተነሣ በዚያ ሥርዓት ውስጥ ሆኖ በፍጹም ሊያመልጡት የማይቻል መሆኑን አያሳይም ?
ለምሳሌ ማርካኪስ ካህናትን “non-productive class” (አምራች ያልሆነ መደብ) ሲል ይገልጣቸዋል ።[8] ካህናትን ለምሳሌ አነሣሁ እንጂ አስተዳዳሪዎች ፣ ገዢዎች ፣ ዳኞች ፣ ወታደሮች ፥ ብቻ ገበሬ ያልሆነ ሁሉ ለእሱ “አምራች” አይደለም ። ለእሱ ካህናት መማራቸውም ሆነ ማስተማራቸው ፣ በቅዳሴ ፣ በማኅሌት ፣ በሰዓታት ፣ ክርስትና በማንሣት ፣ ጸሎተ ፍትሐት በማድረስ ፣ ጋብቻን በመፈጸም ፥ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ውስጥ በመዳኘት ፣ በማስታረቅ ፣ ወዘተርፈ የሚያደርጉት ሥራ ሁሉ “አምራች” አይደለም – ቁስ አካላዊ ምርትን አያስገኝም – ምግብ ፣ ልብስ ፣ መጠለያ ወዘተርፈ አይሆንም – ስለዚህም “ዋጋ” የለውም ነው ድምዳሜው ። ይልቁንም ክህነታቸው “የብዝበዛ መሣሪያ” ነው ።
“By all accounts, the clergy has always compromised a large class in Ethiopian society. The attraction of the clerical profession in a society whose culture is dominated by religion is obvious. The clergy has enjoyed social prestige, and influence second only to that of the political authority. According to an Amhara proverb, ‘if you work for man, you shall perish; if you work for God, you shall flourish.”[9]
ይህን ያነበበ – ሀገሩን ካላወቀ – እግዚአብሔርን አገለግላለሁ ብሎ ክህነትን የሚቀበል ሰው ያለ አይመስለውም ፤ እበላ ብሎ እንጂ ። ብዙ ገባሮች ከክህነት እና ከደባትርነት ገባርነታቸውን የሚመርጡም አይመስለውም ። “ተማሪ በሞተ በሰባት ዓመቱ ፥ ተምሮ ይመጣል ትላለች እናቱ ።” ተብሎ የተለቀሰበት ሀገር እንደሆነም አይገምትም ። ግን ይህን ሁሉ ለማስረዳት መሞከሩ ምንም ዋጋ የለውም – መነሻው “ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት” እስከሆነ ድረስ እነዚህ ነገሮች ለእሱ ትርጉም ሊኖራቸው አይችልም ። ከቁስ አካል ባሻገር ሌላ ነገር መኖሩን – “ሰው በእንጀራ ብቻ መኖር አለመቻሉን” እስካላሳመናችሁት ድረስ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ መረዳት እና ትንታኔ ሊኖረው አይችልም ። ለዚህም ነው ማርክሳዊ ላልሆነ ሰው ወይም ቢያንስ ቁስ አካልነትን ላልተቀበለ ሰው የፕሮፌሰር ባህሩ ፣ የማርካኪስም ሆነ የሌሎች ምሁራን ትንተና ሲሻል ስንኩል – ሲብስ ስሑት ሆኖ መቅረቱ ግድ የሆነው ። ችግሩ ብዙዎቻችን እንደ ፕሮፌሰር ባሕሩ ሁሉ ከምናነባቸው ትንተናዎች እና ትረካዎች ጋር በቀጥታ መስማማትን ወይም መሟገትን እንጂ ከጀርባቸው ያሉትን መነሻዎች መጠየቅን ጉዳይ አናደርገውም ። እውነታው ፍልስፍናዊ መነሻዎች የሌሉት ፣ ወይም ከእነሱ ተነጥሎ ብቸውን ሊቆም የሚችል ምንም ዓይነት ትንተና አለመኖሩ ነው ። ፕሮፌሰር ባሕሩ ግን ይህን ስተውታል ።
ጸሐፊዎቻችን እንደሚሉት አንዳንድ ተምኔቶች – ፍትሕ ፣ እኩልነት ፣ ዲሞክራሲ ፣ ዕድገት ወዘተርፈ – ምንም ማስረጃ ሳያስፈልጋቸው በጎ ነገሮች ከሆኑ ፥ ወይም ማርክሳዊ ትንተናዎች ከፍልስፍናዊ መነሻዎቻቸው ተለይተው ጥቅም ላይ ሊውሉ ከቻሉ – ማርክስ እና ኤንግልስ ለምንድነው – ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊነትን ለእነዚህ ግቦች እና ትንተናዎች መነሻ አድርገው ያቀረቡት እና ለሶሻሊዝም መመሥረት ይህን መርሕ መቀበል የግድ መሆኑን ያወጁት ? ‘በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ – ለእነዚህ ነገሮች እንታገል’ ማለት በተቻላቸው ነበር – የእኛ ጸሐፍት አሁን እንደሚያደርጉት ።
ከማርክስ እና ከኤንግልስ ጋር ፈጽሞ አልስማማም – ርእዮታቸውንም ሆነ ግቦቻቸውን አልጋራቸውም ። ነገር ግን ይህን በማድረጋቸው አሳቢነታቸውን አደንቃለሁ ። ደግሞም ማስተዋል የሚገባን ፥ ማርክስ እና ኤንግልስ ከዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት ተነሥተው አልነበረም ወደ መዳረሻቸው – ወደ ኮሚዩኒዝም የሔዱት ። በተቃራኒው ነበር እንጂ ። የኮሚዩኒዝም ሐሳብ ከማርክሳዊነት ይቀድማል ። ከማርክስ እና ከኤንግልስ የቀደሙ የኮሚዩኒዝም አራማጆች ነበሩ ። ማርክስ እና ኤንግልስ “ማኒፈስቶአቸው” ላይ እነዚህን ቀደምቶቻቸውን በየዓይነቱ እያነሡ ይተቿቸዋል ።
ነገር ግን የኮሚዩኒዝም ሐሳብ ቀድሞ ቢኖርም – ማርክስ እና ኤንግልስ ይህ ግብ የሚቆምበት ፍልስፍናዊ መሠረት ለመጣል ብዙ ለፉ ። ምን አለፋቸው ? መልሱ ቀላል ነው – ከላይ እንዳሳየነው – ያለ መነሻ ብቻቸውን ሊቆሙ የሚችሉ ግቦች ሊኖሩ እንደማይችሉ ስለተረዱ ነበር ። አንድ ጊዜ ቁስ አካልነትን በሰዉ አእምሮ መትከል ከቻሉ – ሌላው ሁሉ ይከተላል ። አለዚያ ግን ሁሉም ግቦች ተጠየቅ አለባቸው ።
ክርስቲያኖች እንደሚሉት ይህ ዓለም አላፊ ከሆነ እና መንኖ ጥሪት የሚያጸድቅ ከሆነ – “የመደብ ትግል” ለምን ዐቢይ ጉዳይ ይሆናል ። ለሀብታም ሰው መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ከሆነ – “ለከበርቴው መደብ” ኀዘኔታ እንጂ ሌላ ምን ሊሰማን ይችላል ? ሁሉም ነገር እንዲሁ የተገላቢጦሽ ይሆናል ። ማርክስ እና ኤንግልስ ይህን ተረድተዋል ። የኛ ጸሐፍት እና ምሁራን ለምንድነው እየተረዱት ያልሆነው ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ዘወርወር ያለ መንገድ መሔዳችን የግድ ነው ። ለሚቀጥለው ክፍል እናሳድረው ።
[1] አንዳርጋቸው (1992) ፣ መቅድም ፣ ገጽ 3
[2] Engles F. And Marx K. (1975), p. 91
[3] Balsvik R. (2005), Haile Sellassie’s Students: The Intellectual and Social Background to Revolution, 1952-1974. Addis Ababa University Press, Addis Ababa. p. 265
[4] ዝኒ ከማሁ ፣ ገጽ 189-90
[5] ኢሕአፓ (1967) ፣ ጭፍን ፋሺዝም በኢትዮጵያ ነገሠ ። ዲሞክራሲያ ፣ ቅጽ 1 ፣ ቁጥር 17 ፣ ሕዳር 15 ፣ 1967 ዓ.ም. ። (ምንጭ፡ ቀመሪቲ ጨንገሬ እና ሰለሞን ሥዩም (2010) ፣ ዲሞክራሲያ ። ገጽ 134-5)
[6] Bahru (2014), p. 8
[7] Markakis J. (1975), Ethiopia: Anatomy of a Traditional Polity. Oxford University Press, Addis Ababa. p. 3
[8] Ibid, p. 79
[9] Ibid, p. 96






this is best6 idia
It is true that we never ask the phylosophical basis of anything… we are near sighted.
As i grow up, the perception i had was socialism was “working together and eating together, never leaving someone starving” So it was odd when some one says you cant be socialist and Christian… thats because the destination of everyone having what they need seemed like heaven on earth, but when you go deeper and see that GOD is not there, you know its not for you
But as already said, we just see the goals thet align with our perception and not the whole truth…
What was socialism and communism for Ethiopian society that was Christian, that shared what they had for the sake of thie Soul, for a people that never left a stranger to sleep outside…
When one just asks what was the root philosophy, what were the actual goals and directions, we will all know and repent for all the bad we called upon our selves
Thank you for the article