ክፍል ፬ ፡ ወደ ርስታችን ያልተመለስንበት ኢዮቤልዩ

ቀድመን የማርክሲዝምን መነሻዎች ለመዳሰስ ሞክረናል ። እነዚህ መነሻዎች ላይ ብዙ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎች ሊነሡ ይችላሉ – ተነሥተውማል ። እኔ ግን እንዳልሁት አላማዬ ማርክሲዝም ከመሠረቱ የተሳሳተ ርእዮት መሆኑን ማሳየት ስላልሆነ ፣ ጥልቅ ወደሆነ ፍልስፍናዊ ሙግት አልገባሁም ። ከፊታችን አማኝ የሆነ ማርክሳዊ የለም – አማኝ የነበሩትም ክደዋል ። ስለዚህ ለማን ነው የማርክሳዊነትን ስሑትነት የምናሳየው ?

ነገር ግን ባለፈው ምዕራፍ ያነሣነውን ጥያቄ ለመመለስ የማርክሳዊነትን ተፈጥሮ በተመለከተ አንድ ልብ ማለት ያለብን ነገር አለ ። በመጀመሪያ በጽሑፋችን ሁለተኛ ምዕራፍ በአጭሩ የማርክሳዊነትን መሠረታውያን ለመቃኘት ስንሞክር ጠቆም እንዳደረግነው ማርክሳዊነት ውስጥ ለመረዳት የሚቸግር ፥ ለማስታረቅም የማይቻል አንድ ቅራኔ አለ ።

በአንድ በኩል ማርክሳዊነት “ሳይንሳዊ” ነኝ ማለቱ አለ ። ይህንም ሲል ከላይ እንዳነሣነው – አንድ የፊዚክስ ወይም የባዮሎጂ ባለሙያ ተመራምሮ የተፈጥሮን ሕጎች እንደሚያውቀውና እንደሚያሳውቀው ሁሉ ፥ ኮሚዩኒስቶችም እንዲሁ ለራሳቸው የሰጡት ሚና  የዓለምን ሥሪት – ቁስ አካልን – እና የሚገዙትን ሕጎች በማጤን – ያለፈውን ፣ እየሆነ ያለውን እና ወደፊት የሚሆነውን መግለጥ ነው ። በተለይ ያለው ነገር ሁሉ  (ሰውንም ፣ ሐሳብንም ፣ ኅሊናንም ጨምሮ) ቁስ አካል ነው ብለው መነሣታቸውን ስንመለከት እና ቁስ አካል ደግሞ በተወሰኑ ሕጎች እንደሚገዛ ማሰባቸውን ስንመለከት  የሐሳባቸው መደምደሚያ determinism (ውሱንነት ?) እንዲሆን እንጠብቃለን ። እነሱም አያሳፍሩንም ። ያለፈውን ታሪክም ሆነ ወደፊት የሚመጣውን – ጥርጥር በሌለበት እርግጠኝነት ምን ከምን እንደሚከተል እየተነተኑ ያስረዱናል ። በመጨረሻም “የከበርቴው መደብ መገርሰስ እና የወዛደሩ መደብ ድል ማድረግ ሁለቱም አይቀሬ ናቸው ።” ይሉናል ።[1]

ማርክስና ኤንግልስም ሆኑ እነሱን እየጠቀሰ ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነትን የሚያብራራው ስታሊን ፥ ሐሳቦችም ጭምር የቁስ አካላዊ ሁኔታ ውጤቶች እንደሆኑ ደጋግመው ይገልጣሉ ። ስለዚህ በዘመኑ ባርነት ፣ በዘመኑም ፊውዳሊዝም ከክፋት የመነጩ እኩያት ሳይሆኑ – ከማኅበረሰቡ ቁስ አካላዊ ሁኔታ ፣ የምርት ዕድገት ደረጃ – የመነጩ ሐሳቦች ናቸው ። የዳያሌክቲክስ ውጤት ናቸው ። በዚሁ መንገድም ለቀጣዩ ሥርዓተ ማኅበር ቦታ መልቀቅ ሲኖርባቸው ለቅቀዋል – እንዲህ እያለም ኮሚዩኒስታዊ ሥርዓት እስኪመጣ እና የመደብ ልዩነት እስኪጠፋ ድረስ ይቀጥላል ። (አንድ መልስ ላገኝ ያልቻልሁለት ጥያቄ ቢኖር – ‘ኮሚዩኒዝም ሲመጣ ዳያሌክቲክስ ይቆማል ወይ ?’ የሚለው ነው – ምክንያቱም በመርሑ መሠረት መቆም አይችልም ፤ ግን ደግሞ መደቦች ከጠፉ እና ተፈጥሮም በሰው በቁጥጥር ስር ከዋለች ቅራኔው በማን መካከል እና ወዴት ሊቀጥል ይችላል ?)

“Does it require deep intuition to comprehend that man’s ideas, views and conceptions, in one word, man’s consciousness changes with every change in the conditions of his material existence, in his social relations and in his social life?

“What else does the history of ideas prove, than that intellectual production changes its character in proportion as material production is changed? The ruling ideas of each age have been the ideas of its ruling class.”[2]

“It is not the consciousness of men that determines their being but, on the contrary, their social being that determines their consciousness… Just as our opinion of an individual is not based on what he thinks of himself, so can we not judge of a period of transformation by its own consciousness; on the contrary, this consciousness must be explained rather from the contradictions of material life, from the existing conflict between the social productive forces and the relations of production. No social order ever disappears before all the productive forces for which there is room in it have been developed; and new, higher relations of production never appear before the material conditions of their existence have matured in the womb of the old society itself. Therefore, mankind always sets itself only such tasks as it can solve; since, looking at the matter more closely we will always find that the task itself arises only when the material conditions necessary for its solution already exist or are at least in the process of formation.[3]

እንዲህ ዓይነት አባባሎቻቸው ውስጥ አንድ ዓይነት ‘ገለልተኝነት’ – dispassion እንመለከታለን ። “የሚሆኑትን ነገሮች እናውቃቸዋለን – መሆናቸው ደግሞ አይቀርም ።” ከዚህ አንጻር ፣ ኮሚዩኒስቶች ማንንም ወዳጅ ፣ ማንንም ጠላት የሚያደርጉ አይመስለንም ። ምክንያቱም ሁሉም ሰው – ባሪያውም ጌታውም ፣ ባለመሬቱም ጭሰኛውም ፣ ከበርቴውም ወዛደሩም ፣ ወንዱም ሴቷም – የሚያስቡትን የሚያስቡት ፣ የሚናገሩትን የሚናገሩት ፣ የሚያደርጉትንም የሚያደርጉት ራሳቸውን ካገኙበት ቁስ አካላዊ ሁኔታ – ከተገኙበት የምርት ሥርዓት እና በዚያ ሥርዓት ውስጥ ካላቸው ቦታ የተነሣ ነው ። በዚያ ሁኔታ ውስጥ እስከ ተገኙ ድረስ በተለየ መንገድ የማሰብ ፣ የመናገር እና የመወሰን አቅሙ የላቸውምና ።

አንድም ልክ አንድ ፍሬ በስሎ ከተንጠለጠለበት ቅርንጫፍ ተበጥሶ ወደ መሬት መውደቁ ጥሩ ወይም መጥፎ ነው እንደማንለው ሁሉ – የማርክሲዝምን መነሻዎች ለተቀበለ ሰው በማኅበረሰብእ ሕይወት ውስጥ የሚሆኑ ነገሮችም እንዲሁ መሆን የለባቸውም ? ሁሉም ነገር ቁስ አካል ስለሆነ እና የተወሰኑ ሕጎችን ስለሚከተል – የሚሆነው ስለሚሆን እና ከዚህ ውጭ ምንም ነገር ስለሌለ – ጥሩ እና መጥፎ የሚሉት ቃላት በዚህ ዓውድ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል ?

በምድር ሆድ ውስጥ የታፈነ እና የቀለጠ ድንጋይ ፣ በመጨረሻ ሲፈነዳ እና የምድርን ገጽ ሲያጥለቀልቅ ፣ በዚህ ውስጥ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ የራሱ ፈቃድ ፣ የራሱ ጥረት እንደሌለ ሁሉ “ዐብዮት” ሲፈነዳ እና የወዛደሩ መደብ ገዢውን መደብ ሲንደው – በዚህስ ውስጥ ምን ፈቃድ ፣ ምንስ ጥረት አለበት ? ልክ እሳተ ገሞራውን ጥሩ ወይም መጥፎ ልንለው እንደማንችለው ፣ “ዐብዮቱንስ” ምንድነው ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው ? ተኩላው ሚዳቋዋን አሳድዶ ሲበላትስ ማን ‘ክፉ ሠራህ’ ይለዋል – አማራጭ እንዳለው ሁሉ ?

ሁሉም ነገር ቁስ አካል እንደመሆኑ እና ለተፈጥሮ ሕጎች እንደ መገዛቱ ፣ “ሕይወት” ያላቸውን ቁስ አካላት “ሕይወት” ከሌላቸው ቁስ አካላት የተለየ “ዋጋ” የሚያሰጣቸው ምንድነው ? አይታየኝም ።

ከእነዚህ ነጥቦች በመነሣት ማርክሳውያን ለማንም ቢሆን ጠንካራ ጥላቻ ወይም ፍቅር ይኖራቸዋል ብላችሁ አትጠብቁም ። ፍቅር ፣ ጥላቻ ወይም ሌሎች ስሜቶች የቁስ አካላዊ ሁኔታ ነጸብራቅ አይደሉምን ? ስለዚህ ሌሎች ሰዎች ከበርቴም ሆነ ወዛደር ከቁስ አካላዊ ሁኔታቸው የተነሣ እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ ። የታሪክን አካሔድ እና የቅራኔን ሕጎች ስለማያውቁ ራሳቸውን ያገኙበት ሁኔታ የሚያሳድርባቸውን ስሜት ማስተናገዳቸው የግድ ይመስላል ። ለወዛደሩ ከበርቴው እሱን የሚጨቁነው እና የሚያስጨንቀው “ራሱን ከሚያገኝበት ቁስ አካላዊ ሁኔታ” የተነሣ መሆኑ አይታወቀውም ። ስለዚህ የመራቡን እና የመጠማቱን ምሬት ሁሉ ከበርቴው ላይ ያነጣጥረዋል ።  ኮሚዩኒስቶች ግን የታሪክን እና የቅራኔን ሕጎች የተረዱ እንደመሆናቸው መጠን ፣ ተመሳሳይ ስሜት እንዲያሳድሩ አይጠበቅም ። በተለይ ደግሞ መሪ የሆኑት ኮሚዩኒስቶች ራሳቸው ከከበርቴው መደብ የተገኙ መሆናቸውን ስንመለከት ወዛደሩ ጋር ያለው ከመገፋት የሚመነጭ የግል ምሬት እና ብሶት በእነሱ ላይ እንዲታይ አንጠብቅም ። ለእነሱ ጉዳዩ ወደኋላ ሊመልሱት ከማይቻለው የታሪክ ሒደት ጋር አካሔዳቸውን የማስተካከል ጉዳይ ነው ። በዕውቀታቸው ምክንያት የዕለቱን ጉዳይ አይደለም የሚያስቡት – ትልቁን ስዕል እንጂ – የማይቋረጠው የመደቦች ትግል ። ቅራኔው የግል አይደለም – የታላቁ ተፈሮአዊ ቅራኔ አንድ መገለጫ እንጂ ።

በዚህ የታሪክ ሒደት ውስጥ የራሳቸውን ሚና ለመወጣት ፥ ዐብዮታዊውን ሒደት ለማፋጠን እና ለማሳለጥ ተጨቋኙን ለጭቆናው “የማንቃት” ፣ ምሬቱን የማነሣሣት ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ። ጭቆናውን ዕድሌ እና ዕጣዬ ነው ብሎ እንዳይቀመጥ ፈጥኖ እንዲነቃ ሊያደርጉት ይችላሉ – መንቃቱ ባይቀርም ቅሉ ። እነሱ ራሳቸው ግን በዚያ ስሜት የሚዋጡበት ምን ምክንያት ይኖራል ?

በቅድሚያ የዐብዮቱ መምጣት እንዲፋጠን ማድረግ እንችላለን ብለው ማሰባቸው ችግር ያለበት ነው – ከዳያሌክቲክስ ሕግጋት ውጭ በእነሱ “ፈቃድ” የሚሆን ነገር እንዳለ ሁሉ ።

ዳግመኛም የዐብዮቱ መምጣት እንዲፋጠን የሚፈልጉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ። “ዐብዮቱ ይመጣል” ከማለት ባለፈ “ዐብዮቱ መምጣት አለበት ።” ማለታቸው ከምን ይመነጫል ? ለምሳሌ ጓድ ኃይሌ ፊዳ ጂኦሎጂስት እንደ መሆኑ “እሳተ ገሞራ ይፈነዳል ።” የሚል ዕውቀቱን ሊያጋራን ይችላል ። ነገር ግን “እሳተ ገሞራው ፈጥኖ መፈንዳት አለበት ።” ሊል ይችላል ? እሳተ ገሞራው ቶሎ እንዲፈነዳም ራሱን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ሊደርስ ይችላል ?

ዶክተር አክሊሉ ለማ እንዶድ ቢልሃርዚያን እንደሚያጠፋ ማስተዋላቸው አንድ ነገር ነው ። እንዶድን እንደ መድኃኒት ሲያዩት ግን ከባይዮሎጂስትነታቸው ድንበር ይሻገራሉ ። እንዶድ ቢልሃርዚያን ከማጥፋቱ ተፈጥሮአዊ ሕግ እና እውነታ ባለፈ – የሰው መታመም መጥፎ እንደሆነ ፣ ከሕመም መዳኑም ተፈላጊ ነገር መሆኑን እየተናገሩ ነው ። ባዮሎጂ ውስጥ ይህን እንዲያውቁ የሚነግራቸውም ሆነ የሚያስገድዳቸው ምንም ነገር የለም ። ከባዮሎጂ አንጻር በሰውና በቢሊሃርዚያ ትል መካከል ምን መበላለጥ አለና ነው – ሰው እንዳይታመም ሲባል የቢሊሃርዚያ ትሎች መጥፋት ያለባቸው ? ሁለቱም ሕያዋን ፥ ሁለቱም ሥጋና ደም ። ማንኛውም ሰው አንድ ነገር ሆኗል ፣ ወይም ይሆናል ከማለት አልፎ መሆን ነበረበት ፣ ወይም አልነበረበትም ፣ አለበት ወይም የለበትም ሲል – ሳይንቲስትነቱ እዚያ ጋር ያበቃል ። አሁን ወይ ከሞራል ሕግ አንጻር ፣ አሊያም ከራሱ ፍላጎት አንጻር ነው እየተናገረ ሊሆን የሚችለው ።

ዐብዮታውያን በተለይ ከከበርቴው ወገን የተገኙ ሲሆኑ – ዐብዮቱ መፈንዳቱን ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር ሊፈልጉት አይችሉም ። በቁስ አካላዊነት እና በምርት ሕግጋት መሠረት ዐብዮት በመፈንዳቱ እነሱ የተሻለ የምርት ተጠቃሚነት አይኖራቸውም ። ስለዚህ ምናልባት ዐብዮቱ በሕይወታቸው ዘመን ሊያመልጡት የማይችሉት ሆኖ ፊት ለፊት ካልመጣባቸውና ከጥፋት ለማምለጥ ብቸኛው መንገድ ከዐብዮቱ ጋር ከመቃረን ይልቅ የዐብዮቱን መስመር መቀላቀል ነው ብለው ካላሰቡ በስተቀር መደባቸውን ለመክዳት ምን ምክንያት ይኖራቸዋል ? ማርክስና ኤንግልስ ራሳቸው አይደሉም ከቁሳዊ ራስ ወዳድነት ውጪ ያሉ የግንኙነት ገመዶችን ሁሉ ሐሰተኛ እና ከንቱ መሆናቸውን የነገሩን ?

“The bourgeoisie, historically, has played the most revolutionary part.

“The bourgeoisie, wherever it has got the upper hand, has put an end to all feudal patriarchal, idyllic relations. It has pitilessly torn asunder the motley feudal ties that bound man to his “natural superiors”, and has left remaining no other nexus between man and man than naked self-interest, than callous “cash payment”. It has drowned the most heavenly ecstasies of religious fervor, of chivalrous enthusiasm, of philistine sentimentalism, in the icy water of egotistical calculation. It has resolved personal worth into exchange value, and in place of the numberless indefeasible chartered freedoms, has set up that single, unconscionable freedom – Free Trade. In one word, for exploitation, veiled by religious and political illusions, it has substituted naked, shameless, direct, brutal exploitation.”[4]

ማርክስ እና ኤንግልስ በዚህ አባባላቸው የከበርቴውን መደብ እያመሰገኑት አይደለም ። ነገር ግን ወደ ዓብዮቱ እንደርስ ዘንድ የወዛደሩ መደብ በከበርቴው መደብ ወደዚህ ደረጃ መገፋቱ የግድ ነው እያሉ ነው ። ከዚህ ትንቢት “ሳይንሳዊነት” አንጻር – ይህን በሚያደርገው ከበርቴ ላይ የተለየ የምሬት ስሜት ሊያሳድሩ አይገባም – ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ነውና ። ሁሉም የራሱን ፍላጎት ሲያሳድድ በሚፈጠረው ቅራኔ አይደለም ዐብዮት የሚወለደው ? በዚህ ሒደት ውስጥ ከሁሉም መደቦች ተለይተው የራሳቸውን ፍላጎት ትተው ለሌላው ፍላጎት በመቆም የተፈጥሮን ሕግጋት ሲያዛቡ የምናገኛቸው ዐብዮታውያኑን ብቻ ነው ። በብዙ ዐብዮታውያን ዘንድ የታየው “ለዐብዮቱ ራስን የመሠዋት” መርሕ በዳያሌክቲካዊ እና በታሪካዊ ቁስ አካላዊነት ሐተታዎች ውስጥ ተፈልጎ አይገኝም ። ዞሮ ዞሮ ማንስ ቢሆን መሆኑ ለማይቀረው ፣ መሆኑ አማራጭ ለሌለው ነገር ፣ ሊያፋጥነው ወይም ሊያዘገየው ለማይችለው ነገር የራሱን ፍላጎት እና ሕይወት ይሠዋል ? የሚያሳዝነው ነገር ይህ “መሥዋዕትነት” መሥዋዕትነት ተብሎ ሊጠራ አለመቻሉ ነው ። ምክንያቱም የማንም ጥረትም ሆነ ሞት በመጨረሻው ውጤት ላይ ምንም ተጽዕኖ ሊያሳርፍ አይችልምና ። በረኛውን አልፋ ወደ ግቡ እየተንደረደረች ያለችውን ኳስ መልሶ በመምታት ለጎሉ መግባት አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚሰማውን ተጫዋች ምን ይሉታል ? በተለይ ደግሞ ይህን ለማድረግ ጉዳትን ጭምር እስኪያስተናግድ ድረስ የሚሔድ ከሆነ ። ድርጊቱ ትርጉም አልባ ነው – ትርጉም ይበጅለት ቢባልም – ከጀብደኝነት ያለፈ ስም ሊሰጠው አይችልም ። የተፈጥሮን እና የሰውን የታሪክ መነሻ እና መድረሻ ጠንቅቀው የተረዱት ኮሚዩኒስቶች ይህን ከማንም በላይ ይረዳሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው ። የሚያስበውን የሚያስበው ፣ የሚፈልገውን የሚፈልገው ፣ የሚያደርገውን ሁሉ የሚያደርገው ፣ የሚሆነውንም የሚሆነው ካለበት እና ራሱን ካገኘበት ቁስ አካላዊ ሁኔታ ነው ብለው ከበርቴውን ከመጥላት ፥ ወዛደሩን ከመውደድ አይመለሱም ። ይልቁንም ጥላቻቸውም ሆነ ውዴታቸው ደግሞ እጅግ የጠነከረ ነው ። ከበርቴዎችን ሲያስፈልግ በኃይል ማጥፋታቸው ፣ ማጥፋት ሳያሻቸው ደግሞ ንብረታቸውን መውረሳቸው እኮ ችግር የለውም – ልክ የከበርቴው ሚና መበዝበዝ እንደነበረው ሁሉ – የእነሱ ሚና ብዝበዛውን ማስቆም ስለሆነ ድርጊታቸውን እንረዳዋለን ። ነገር ግን ስሜታዊነቱ ለምን ? ከወዛደሩ ጋር በፍቅር መውደቃቸውም እንዲሁ ግልጽ አይደለም – እንደ ከበርቴው ሁሉ ራሱን በዚያ ሁኔታ አገኘው እንጂ ሐሳቡ እና ሥራውም ከቁስ አካላዊ አዃዃኑ መነጨ እንጂ መርጦ ያደረገው ነገር አይደለምና ። ከሁሉም በላይ ግን የወሰዱትን ሚና መውሰዳቸው በራሱ የማይፈታ እንቆቅልሽ ነው ፤ ከዳያሌክቲካል ቁስ አካላዊነት ውስጥ ይህን የራስን ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ትቶ ራስን ለሌሎች የመሠዋት መርሕ ልናወጣው አንችልምና ።

የማርክስ እና የኤንግልስ ማኒፌስቶ ውስጥ ከላይ ከገለጥነው “ሳይንሳዊ” ‘ገለልተኝነት’ ጎን የሚከተለውን በስሜት የተሞላ ሐተታ እናገኛለን ።

“Abolition of the family! Even the most radical flare up in this infamous proposal of the communists. On what foundation is the present family, the bourgeois family, based? On capital, on private gain. In its completely developed form this family exists only among the bourgeoisie. But this state of things finds its complement in the practical absence of the family among the proletarians, and in public prostitution.

“The bourgeois family will vanish as a matter of course when its complement vanishes, and both will vanish with the vanishing of capital.

“Do you charge us with wanting to stop the exploitation of children by their parents? To this charge we plead guilty…

“The bourgeois clap-trap about the family and education, and about the hallowed co-relation of parent and child, becomes all the more disgusting, the more, by the action of Modern Industry, all family ties among the proletarians are torn asunder, and their children transformed into simple articles of commerce and instruments of labor.

“But you communists would introduce community of women, screams the whole bourgeoisie in chorus.

“The bourgeois sees in his wife a mere instrument of production. He hears that the instruments of production are to be exploited in common and naturally can come to no other conclusion than that the lot of being common to all will likewise fall to the women.

“He has not even the suspicion that the real point aimed at is to do away with the status of women as mere instruments of production.

(አንድ ጊዜ ላቋርጣቸውና ፥ ማርክስ እና ኤንግልስ እዚህ ጋ ምን እያሉን ነው ? ሕፃናትና ሴቶች ከሰውነታቸው ወደ ሸቀጥነት “ዝቅ ተደርገዋል” እያሉን ነው ? ግዑዝ ከሆነው ቁስ አካል ወይም ከእንስሳት ተለይተው የተለየ ህላዌ ፣ አንዳች ልዕልና አላቸው እያሉን ነው ? አሁንም ይህን የሰው ልጅ ልዩ ክብር እና ልዕልና[5] በዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት ውስጥ እንፈልገዋለን ። ነገር ግን አናገኘውም ። ማርክስ እና ኤንግልስ ይቀጥላሉ ።)

“For the rest, nothing is more ridiculous than the virtuous indignation of our bourgeois at the community of women which, they pretend, is to be openly and officially established by the Communists. The Communists have no need to introduce community of women; it has existed almost from time immemorial.

“Our bourgeois, not content with having the wives and daughters of their proletarians at their disposal, not to speak of common prostitutes, take the greatest pleasure in seducing each other’s wives.

“Bourgeois marriage is in reality a system of wives in common and thus, at the most, what the communists might possibly be reproached with, is that they desire to introduce, in substitution for a hypocritically concealed, an openly legalized community of women. For the rest, it is self-evident that the abolition of the present system of production must bring with it the abolition of the community of women springing from that system, i.e., of prostitution both public and private.”[6]

እዚህ ውስጥ “ከሳይንሳዊነት” እና ከቁስ አካልነት ፣ ከምርት ተጠቃሚነት ያለፈ – ከፍ ያለ ነገር ይደመጣል – የሞራል ቅንዐት ፣ በበሰበሰ ምግባር ላይ የሚደረግ ቁጣ – profound moral outrage, moral indignation ። ይህ ቁጣ እና ቅንዐት ኒውተን ዛፍ ሥር ተቀምጦ አንዲት ፍሬ ከዛፉ ላይ መውደቋን በማየት የመሬት ስኅበት እንዳለ ከማስተዋሉ ጋር ልናዛምደው እንችል ይሆን ? እንቸገራለን ። ይልቁንም ይህን ቅንዐት እና ቁጣ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡን አክአብን ስለ ናቡቴ ደም እግዚአብሔር እንደሚበቀለው ፣ ደሙንም ውሾች እንደሚልሱት ሲነግረው ድምፁ ውስጥ የምንሰማው ይመስለኛል ። ናቡከደነፆር በግድግዳ ላይ ተጽፎ ባየው መልእክት ውስጥ የምናነበው ይመስለኛል ። ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በተላከው መልእክት ውስጥ የምናደምጠው ይመስለኛል ። ይህ ቁጣ ፣ ይህ ቅንዓት ፥ የዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት “ሳይንሳዊነት” ሊያመነጨውም ሆነ ሊሸከመው የሚችለው አይደለም ። ይህ ቁጣ ከሰው ልጅ “ቁስ አካላዊ ሁኔታ” እና “የምርት ተጠቃሚነት” የሚመነጭ “ቁስ አካላዊ ሐሳብ” አይደለም ። ከቁስ አካልም ሆነ ቁስ አካል ከሚገዛላቸው ሕጎች በላይ ነው ። ታዲያ ማርክስ እና ኤንግልስ ከወዴት አመጡት ?

ይህ ብቻም አይደለም ። ከላይ እንዳነሣነው ኮሚዩኒስቶች በከባድ ናፍቆት እና መጠባበቅ የተሞሉ ናቸው ። ‘ዐብዮቱ መምጣቱ ስለማይቀር’ ብለው ግድ የለሽ አይሆኑም ። መምጣቱን በጉጉት ይጠባበቃሉ ፣ ይመጣ ዘንድም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። ስለ ዐብዮቱ እና ይመጣ ዘንድ ስለሚደረገው ትግል ፣ ስለ ሚከፈለው ዋጋ ፥ እሱን ተከትሎ ስለሚገነባውም ኅብረተሰብአዊ ሥርዓት ግጥም ይገጥማሉ ፣ መዝሙር ይጽፋሉ ፣ ልብ ወለድ ታሪኮችን ይደርሳሉ ። ማርክስን ፣ ኤንግልስን ሌሎቹንም የቀደሙ “ዐብዮታውያን አባቶች” ያደረጉትን ሁሉ ከቁስ አካላዊ ሁኔታቸው የተነሣ እንዳደረጉ ሰዎች ሳይሆን – ለሌላው ጥቅም የቆሙ እና ራሳቸውን “ለተቀደሰ” ዓላማ የሰዉ ልዩ ሰዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል ። ስዕሎቻቸውን በግድግዳ ላይ ያኖራሉ ። በጭራሽ ሊስቱ እንደማይችሉ አድርገው ያስቧቸዋል ። እነሱም እንደ ሌላው ሁሉ “ከቁስ አካል ብቻ የተሠሩ” ናቸው ብሎ ለማመን እስከሚያስቸግር ድረስ ። እንዲህ ያሉት ስሜቶችስ እንዴት የዳያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት ከሚጋብዘው ‘ገለልተኝነት’ ፣ አለኝ ከሚለው “ሳይንሳዊነት” ጋር ይታረቃሉ ?

እነዚህ ቅራኔዎች (የማርክሳውያንን ቋንቋ ለመጠቀም) “ሊታረቁ የሚችሉ አይደሉም ።” ግን በሚገርም ሁኔታ ማርክስ እና ኤንግልስም ይሁኑ ከእነሱ በኋላ የመጡት ተከታዮቻቸው በእነዚህ ሐሳቦቻቸውን እና ድርጊቶቻቸውን ሁሉ ትርጉም አልባ በሚያደርጉ ቅራኔዎች አልተረበሹም ። እንዴት ላይረበሹ እንደቻሉ አላውቅም በእውነቱ ። ነገር ግን መጠየቅ ያለብን ወሳኝ ጥያቄም አለ ።

ማርክሳዊነት ይህን ከራሱ ፍልስፍናዊ ምንጮች ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ስሜታዊነት ፣ የሞራል ስሱነት እንዲሁም ጉጉት እና ናፍቆት ከወዴት አገኘው ?

ይህን ጥያቄ የማነሣው ፣ ማርክሳዊነት “ቢያልፍበትም” – ተዋሥኦዎቻችን ግን ማርክሳዊ ግቦችን ማዕከል ማድረጋቸው ፥ እንዲሁም ማርክሳዊ ፅንሰ ሐሳቦች ላይ መንጠልጠላቸው ለምንድነው የሚለውን ለመመለስ ይህን ጥያቄ መመለሳችን ስለሚረዳን ነው ። በተጨማሪም የማርክሳዊነት ቁስ አካላዊ መነሻዎችም ሆኑ ከእነዚህ መነሻዎች ጋር የሚቃረኑት ስሜታዊነቱ ፣ የሞራል ስሱነቱ እንዲሁም ለሚመጣው መደብ አልባ ማኅበረ ሰብእ ያለው ጉጉት እና ናፍቆት ማርክሳዊነት በተቀመረበት ወቅት ላይ ከነበረው ምሁራዊ እና ሞራላዊ ከባቢ (intellectual and moral environment) ጋር መዛመዱን ማወቃችን ማርክሳዊነት ወደ እኛ ሀገር ታሪክ የመግባቱን እና የመውጣቱን (ወይም ወጥቶ ያለመውጣቱን) ነገር ለማብራራት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ። እናም እንደ ጠፋሁ ሳታስቡ ታግሳችሁ ተከተሉኝ ።

[1] Engels F. and Marx K. (1975), p. 60

[2] Ibid, p. 72

[3] Stalin J. (1975), p. 40 (quoting Marx)

[4] Engels F. and Marx K. (1975), p.44-5

[5] ጉዳዩን ላለማወሳሰብ ነው እንጂ – ማርክሳዊነት ውስጥ ፈልገን የማናገኘው ሌላው ነገር የሰውነትንም (humanity) ሆነ የግለሰብነት (individuality) ፅንሰ ሐሳብ ነው ። ለምሳሌ ሰዎች እንደሌላው ሁሉ ነገር ቁስ አካል ሆነው እና ለቁስ አካል ሕግጋት የሚገዙ ሆነው ሳለ – ከተፈጥሮ ውጭ ሆነው የሚቆጠሩት ለምንድነው ። በሰውና በተፈጥሮ መካካል ቅራኔ አለ ስንል ሰውን ከተፈጥሮ እየለየነው አይደለምን ? ነገር ግን የትኛው የቁስ አካል ሕግ ነው ለሰው ይህን ልዩ መሆነ ያጎናጸፈው ? ከዚህም አለፍ ስንል እያንዳንዱን ሰው የተለየ ሕልውና የሚሰጠው – ግለሰብ የሚያደርገው ነገር ግምን እንደሆነ አናውቅም ። በክርስትና ውስጥ ለምሳሌ ነፍስ የሚለው ፅንሰ ሐሳብ እያንዳንዱ ሰው የተለየ ህላዌ ያለው መሆኑን ያስረግጣል ። ነገር ግን በማርክሳዊ እሳቤ ውስጥ ነፍስ የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም – ምክንያቱም ነፍስ ተፈጥሮዋ ረቂቅ ስለሆነ እና ማርክሳዊነት ደግሞ የረቂቃንን ህልውና ስለማይቀበል ። ስለዚህ ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን – የተለየ ህልውና እንዳላቸው አድርገን ለማሰብ የሚያስችለንን መሠረት ማርክሳዊነት ውስጥ አናገኘውም ።

[6] Ibid, p. 67-71

Share...

Facebook
Telegram
WhatsApp
X
Email
Print
Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Posts

Emmaus Posts
በርናባስ ሽፈራው

“የአእላፋት ዝማሬ”

ሁለተኛው የአእላፋት ዝማሬ ባለፈው ዓመት በልደት ዋዜማ ተካሔደ ። በአዘጋጆቹ እና በተሳታፊዎቹ ዘንድ ይህ ሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው ዙር በላይ ያማረ እና የሠመረ ሆኖ ተቆጥሯል ። በጠቅላላው ከምእመናን በኩል በተሳትፎም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ያገኘው ተቀባይነት ሌሎች ሁነቶች ሲሆኑ እንደምናየው በጅምር የሚቀር ሳይሆን እንደ ባህል የመተከል ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያመላክታል ። እንዲያውም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሌሎች ቦታዎችም እንዲሰፋ የሕዝብ ጥያቄ እና በአዘጋጆቹም በኩል እቅድ መኖሩ ይታወቃል ። ስለዚህ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ልክ እንደ ጥምቀት ሁሉ በሁሉም ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ (የአዘጋጆቹ አቅም በፈቀደው ልክ) የአእላፋት ዝማሬ የልደት በዓል መለያ ሆኖ እንዲካሔድ መጠበቅ እንችላለን ። ይህ ነገር በብዙዎች ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ጥቅም የሚሰጥ ሆኖ ይታያል ። በእነርሱ ዐይን ይህ ሁነት ቤተ ክርስቲያን በብዙዎች ዘንድ እንድትታወቅ ያደርጋል ። ብዙዎች በዓሉን አስመልክተው ከሚሔዱባቸው የማይገቡ ዓውዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ከማድረጉ ባሻገር ፥ በቤተ ክርስቲያን ሱታፌ ያላቸውንም በሚስብ እና በሚገባቸው መልኩ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ እንዲያውቋት ያስችላቸዋል ። ስለዚህም የሌሉትን በመጥራት ፥ ያሉትንም በማጽናት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን እንድትዋጅ የሚያስችላት መሣሪያ ነው ፤ ከእርሷ ዘንድ ወደ ክሕደት እና ወደ ኑፋቄ የፈለሰውን ፥ ወይም በስም ክርስቲያን ሆኖ እና ማዕተብ አስሮ ሳለ በምድራዊ ተድላ ባሕር የሰጠመውን ወጣት ወደ ራሷ የምትስብበት መረብ ነው ። ነገር ግን ከኖረው የቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ አንጻር ከመረመርነው ፥ ይህ ሁነት

Read More »
Emmaus Posts
ኤልያስ ገብረ ሥላሴ

መከራ ፣ እከይ እና ክርስትና

መከራ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ድንገተኛ የሆነ ክስተት አይደለም ። ፍቅር በሆነው እግዚአብሔር ለጥቅማችን የሚፈቀድ የእርምት መንገድ ነው እንጂ ። በየዘመኑ ቤተክርስቲያን በወቅታዊ ሁነቶች እንድትወጠር እና መሠረታዊ ነገሮች ትኩረት እንዳያገኙ የሚቀርብ ፈተና አለ ። ሰበር ዜናዎች ፣ ወቅታዊ አጀንዳዎች ፣ አከራካሪ ጉዳዮች ወዘተ ከመነኩሴ መቁጠሪያ በላይ በሚሽከረከሩበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው ። እነዚህ ሁነቶች ትኩረታችንን ይወስዱትና ሳይታወቀን መሠረታዊ ከሆኑትና ዘለዓለማዊነታችንን ከሚበይኑት ጉዳዮች ወጥተን ምድራዊና እዚሁ ቀሪ በሆኑ ጉዳዮች ተወጥረን እንገኛለን ። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁኔታ በቤተክርስቲያንን መምህራን እና “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ላይ እጅግ በርትቶ የሚታይ መሆኑ እና በቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እና መድረኮች ሳይቀር ሰፊውን ሰዓት መያዙ ነው ። የቤተክርስቲያን ተልእኮ ስለ ክርስቶስ ምስክር መሆን ነው ። መሠረታዊ ካልሆኑት ሁነቶች ወጥተን ወደዚህ ዋነኛ ተልእኮአችን እንድንመለስ ተዋሥኦ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ። ይህ በምእመናን ፥ በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲን አገልጋዮች ፥ ዘንድ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው ። የሁነቶችን መሠረት መመርመርና ትክክለኛ ባሕርያቸውን መረዳት ያሻል ። ሁነቶቹ ችግሮች የሆኑ እንደሆነ ሥር ነቀል መፍትሔ ማሰብ የሚቻለው ፥ መልካም አጋጣሚዎችም ከሆኑ በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ ልናውላቸው የምንችለው የሁነቶቹን መሠረት በጥልቀት መረዳት ከቻልን ነው ። በመቀጠልም ተከትለው ሊደረጉ ስለሚገቡ ነገሮች መወያየት ከተቻለ ብቻ ነው ። ካልሆነ አሁን እየሆነ እንዳለው የወቅታዊ አጀንዳዎች አሳዳጅ ብቻ ሆነን ነው የምንቀረው ። በተለይ ዘመናችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ስለሆነ በዚህ

Read More »
Emmaus Posts
መሐሪ ዘመልአክ

ከእውነት አልባነት ጋር የሚካሔድ ሙግት

(‘ሐሳቦች መዘዝ አላቸው’ በሚል ርእስ በኤማሁስ መጽሔት ቅጽ 1 ፣ ቁጥር 1 በወጣው ጽሑፍ ላይ የተጻፈ አስተያየት) በመሐሪ ዘመልአክ (PhD) ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመታት በፊት የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‘የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ’ ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኹ በኋላ ጸሐፊውን ከዚያ በፊት አለማወቄ ገርሞኝ እንደነበር አስታውሳለኹ ። ማን ናቸው ? እንዴት እስከዛሬ ድረስ ስለእርሳቸው ሳልሰማ ቀረኹ ? ለምን ? ይኼ በ1956 ዓ.ም. የታተመ የሬድዮ ንግግር ከኾነ መጽሐፍ ለመጻፍ ብለው ተነሥተው ቢጽፉ ኖሮ ምን ሊጽፉ ነበረ ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች ጭንቅላቴ ውስጥ ተመላልሰዋል ።[1] በኋላ ፈላስፋው ኦርቶዶክሳዊ አማኝ ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተማሪና መምህር እንደነበሩ ስሰማ በመጽሐፉ ውስጥ ያየሁት የሐሳብ ጥልቀት በዘመኑ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልሒቃን ዘንድ የነበረው ተዋሥኦ ሊደርስ ይንጠራራበት የነበረውን ልክ የጠቆመኝ መሰለኝ ። ከዚያ በኋላ ያ የተዋሥኦ ልሕቀት የት ገባ ? እንዴት ድርቅና የተጫነው ተዋሥኦ ዋጠው ? እንዴት ኦርቶዶክሳዊነትን ከአመክንዮ የተፋታ እና አመክንዮን የሚፈራ ጭፍን እምነት የሚያስመስሉ የፎክሎር ሰባኪዎች ተፈለፈሉብን ?  የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህን ለመኾን የሚጠየቀው መስፈርት ስለምን ድፍረት የለበሰ አላዋቂነት መሰለ ? በሚዲያ ላይ ሲናገሩ በአላዋቂነታቸው አንገታችንን የማያስደፉን ካህናት ስለምን ቁጥራቸው አልበረክት አለን ? ኦርቶዶክሳዊነት ችግርን እና ጭንቀትን ለማረሳሳት የተጠመቀ ዕፀ-ዝንጋዔ (‘opium of the masses’) እስኪመስል ድረስ በኦርቶዶክሳዊነት ስም የገነነው ተዋሥኦ ለምን አላዋቂነት ተጫነው ? ቤተ ክርስቲያን ሲባል ከስሜታዊ ሙጥኝታ (sentimental attachment) ባለፈ ለሰው ልጅ ህልውናዊ ጥያቄ የተሰጠ ከሞት ፍርኃት

Read More »
Emmaus Posts
ኤማሁስ

የኤማሁስ መንገድ

መጽሔቷን ለማግኘት ይህን ይጫኑ . . . የዘመናችን ተዋሥኦ በይዘቱም ሆነ በመንገዶቹ በግልብነት በእጅጉ የተጠቃ ነው ። ‘በይዘቱ እንዴት ?’ቢባል ሁነቶች ላይ ያተኮረ እና ወቅታዊነትን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ። አንድም አቋም ከመያዝና ጎራ ከፍሎ ከመናቆር ባለፈ የእውነት የመማር እና የማሰላሰል ጉጉት የማይታይበት በመሆኑ ። በዚህ ተዋሥኦ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሣት እና ከሁነቶቹ የሚሻገር እና ሐሳባዊ የሆነ ትንተና ለማካሔድ መሞከር ትኩረት ያስነሣል ፤ ሲብስም አጉል እንደመራቀቅ ይታያል ። የሚካሄድበት ከባቢ እና ዘመን ደግሞ ሌላ ግልብነት ደርቦለታል ። በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት ፣ ከዘመናዊነትና ከቴክኖሎጂ መራቀቅ ጋር ተያይዞ ሕዝባዊ ተዋሥኦ በጠቅላላው ስለቱን እና ርቀቱን እንዲያጣ ሆኗል ። የሚነበብም ሆነ የሚታይ ወይም የሚደመጥ ነገር አጭር መሆን አለበት ። ነገር ግን ጠቃሚና ወሳኝ ርእሶች እንዲህ ባለ መንገድ ሊስተናገዱ አይችሉም ። የሚያጠግብ ፍሬ ከሌለበት የተመልካቹ እና የአንባቢው ብዛት ምን ጥቅም ይኖረዋል ? እንዲህ ባለው ከባቢ ውስጥ ሁነቶችን ከሁነትነታቸው እና ከሚያመጡት ወቅታዊ ውጤት በተሻገረ መልኩ ለመመልከት እንቸገራለን ። ቀድሞውኑም (እይታችን ከመጥበቡ የተነሣ) ጠባብ አድርገን የቀረጽነውን አጀንዳ በምንገልጽበት መንገድ የበለጠ እናጠብበዋለን ። ነገር ግን ሁነቶችን እና ሒደቶችን ከመሠረታቸው መመርመራችን እና የምናቀርባቸው መፍትሔዎችም እንዲሁ የማይናወጥ መሠረት ያላቸው መሆናቸው አስፈላጊ ከሆነ ተዋሥኦውም እንዲሁ የጠለቀ እና የረቀቀ መሆን አለበት ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ፣ ማንበብ ፣ ማጠናቀር ፣ መወያየት ፣ መሟገት እና እንዲህ ካለው ሒደት

Read More »
Emmaus Posts
በርናባስ ሽፈራው

ክፍል ፭ ፡ ወደ ርስታችን ያልተመለስንበት ኢዮቤልዩ

ሩሲያዊው ደራሲ ፌዮዶር ዶስቶየቭስኪ በ1860ዎቹ አውሮፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኝ የታዘበውን በዘገበበት ማስታወሻው የለንደን ድሆች ቅዳሜ ማታን እንዴት ባለ መንገድ እንደሚያሳልፉ ይነግረናል ። በቅድሚያ ሌሊቱን በሙሉ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ጭምር ደስታ ፈጽሞ በተለየው ፣ ድብርት በተጫነው መንፈስ አኳዃን ሲበሉ እና ሲጠጡ ፣ ከሕይወታቸው መራራነት ለማምለጥ ፣ ራሳቸውን ፍጹም ለማደንዘዝ በሙሉ ጥምብዝ እስኪሉ እንደሚሰክሩ መስማቱን ይዘግባል ። ሳምንቱን ሙሉ ሠርተው የቋጠሯትን ገንዘብ ቅዳሜ ሌሊት እንዲህ ይበትኗታል ። አስከትሎም እንዲህ ባለው አንድ ምሽት እሱ ራሱ በመንደራቸው ውስጥ ሲያልፍ የታዘበውን እና የተሰማውን እንደሚከተለው ይመሰክራል ። “One such night – it was getting on for two o’clock in the morning – I lost my way and for a long time trudged the streets in the midst of a vast crowd of gloomy people, asking my way almost by gestures, because I do not know a word of English. I found my way, but the impression of what I had seen tormented me for three days afterwards. The populace is much the same anywhere, but there all was so vast, so vivid that you almost physically felt things which up till then you had only imagined. In London, you no longer see the populace. Instead, you see a loss of sensibility, systematic, resigned and

Read More »
Emmaus Posts
በርናባስ ሽፈራው

ብያኔን አሳልፎ ያለመስጠት ግዴታ

ከሁለት ሳምንታት በፊት ‘ከጥያቄዎቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች’ በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ አቅርበን ነበር ። ጽሑፉ በዋናነት ማሳነስ (reductionism) የተባለውን ፅንሰ ሐሳብ የሚያነሣ እና የሚተች ነው ። በዚህ ጽሑፋችን ውስጥ መምህር ያረጋል አበጋዝ በቅርቡ ‘ወደ ላይ አያዳልጣችሁ’ በሚል ርእስ ገዳማዊ ሕይወትን ከዘነበ ወላ ዘለፋ ለመከላከል ጽፎ ያጋራውን ጽሑፍ ተችተናል ። ርእሱን በዚህ ጊዜ ጉዳይ ያደረግነውም በዋናነት በምምህር ያረጋል ጽሑፍ ምክንያት ነው ። በተለይ ጽሑፉ ሰፊ ተነባቢነት እና ተቀባይነት ያገኘ እንደ መሆኑ በውስጡ ያየነውን የማሳነስ ዝንባሌ መተቸቱ ጠቃሚ ይሆናል ብለን አመንን ። ነገር ግን የመምህር ያረጋል ጽሑፍ መነሻ ቢሆነንም በይበልጥ ፅንሰ ሐሳቡ ላይ ለማተኮር ነው የሞከርነው – ዓላማችን ነገሩ ላይ ተዋሥኦ እንዲጀመርና የተሻለ መረዳት እንዲፈጠር ማድረግ ስለሆነ ። መምህር ያረጋልም ጽሑፉን ተመልክቶ ምላሽ ሰጥቶናል ። ምላሽ በመስጠቱ ደስ ብሎናል ። በምላሹ ግን አልተደሰትንም ። አለመደሰታችን እኛ በእርሱ ጽሑፍ ላይ ያቀረብነውን ትችት ባለመቀበሉ አይደለም ። ይልቁንም የተሰጠው ምላሽ ከእኛ ትችት ጋር እምብዛም የተያያዘ ባለመሆኑ እንጂ ። ከነገሩ ጋር የማይገጥሙ ምሳሌዎች ቀርበዋል ። ያቀረብነው ሂስ በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል ። በጽሑፋችን በስም ጠርተን ያራቅነው እና ያነወርነው ሐሳብ የእኛ አቋም ተደርጎ ተገልጧል ። “ለቤተ ክርስቲያን ከልባችን ከመጨነቅና ከመቅናት” ተነሥተን “ያልተባለውን ለማስመሰል በመድከማችን” ተወቅሰናል ፤ ዕጣችን ሆኖ “ሳንነቅፍ መጻፍ አልቻልንምና” ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መልስ እና እርማት የሚሹ ሆነው አግኝተናቸዋል ። አንድም ለእኛም ሆነ ለመምህር ያረጋል

Read More »