ኤማሁስ

ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው ቈርሶም ሰጣቸው። ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።

ሉቃስ 24:30-31

ኤማሁስ

ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው ቈርሶም ሰጣቸው። ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ።

ሉቃስ 24:30-31

ለምን ኤማሁስ ተባለ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ኤማሁስ ወደ ምትባል ከተማ በመጓዝ ላይ ወደ ነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ቀርቦ ማንነቱን ሳይገልጥላቸው መጻሕፍትን እየተረጎመላቸው አብሯቸው መጓዙን በሉቃስ ወንጌል የመጨረሻ ምዕራፍ እናነባለን ። በመጨረሻም ኤማሁስ በደረሱ እና ለማዕድ በተቀመጡ ጊዜ እንጀራ ባርኮ ቆርሶ ሲሰጣቸው ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ማንነቱን ይረዳሉ ። ትንሣኤውንም ያምናሉ ። ለኤማሁስ ስያሜ ምክንያት የሆነው ይህ ታሪክ ነው ። ምክንያቱም ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች ወደ ኤማሁስ ባደረጉት ጉዞ ሲነሱ ከነበሩበት ግራ መጋባት እና ተስፋ መቁረጥ በጉዟቸው መጨረሻ ወደ ልቡናዊ ብርሃን እና ፍጹም ሐሴት እንደደረሱ ሁሉ እኛም ዓላማችን ይህን መሰል ጉዞ አድርጎ እነሱ ከደረሱበት መድረስ ስለሆነ ነው ። ይህ ጉዞ አንዳንዶች ተለይተው የሚጓዙበት ሳይሆን የሁሉም ክርስቲያን ጉዞ ነው ። ኤማሁስም ከዚህ የተለየ ህላዌ የላትም ። በኤማሁስ ጉዞ የቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢራት ተገለጡ ። በመጨረሻም ጉዞው በሥጋውና በደሙ ተደመደመ ። ይህም ሁሉ በራሱ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተደረገ ። በጥንታዊቷ ኤማሁስ የሆነው ይህ ሁሉ በዛሬዋም ኤማሁስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይገባዋል ። ይሆናልም ። ኤማሁስ ፕሬስም ለዚህ ነገረ መለኮታዊ ተዋሥኦ መቀጠልና መዳበር ሲባል ወደ መኖር መጣች ።

ለምን ኤማሁስ ተባለ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ትንሣኤው ኤማሁስ ወደ ምትባል ከተማ በመጓዝ ላይ ወደ ነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ቀርቦ ማንነቱን ሳይገልጥላቸው መጻሕፍትን እየተረጎመላቸው አብሯቸው መጓዙን በሉቃስ ወንጌል የመጨረሻ ምዕራፍ እናነባለን ። በመጨረሻም ኤማሁስ በደረሱ እና ለማዕድ በተቀመጡ ጊዜ እንጀራ ባርኮ ቆርሶ ሲሰጣቸው ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ማንነቱን ይረዳሉ ። ትንሣኤውንም ያምናሉ ።

ለኤማሁስ ስያሜ ምክንያት የሆነው ይህ ታሪክ ነው ። ምክንያቱም ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች ወደ ኤማሁስ ባደረጉት ጉዞ ሲነሡ ከነበሩበት ግራ መጋባት እና ተስፋ መቁረጥ በጉዟቸው መጨረሻ ወደ ልቡናዊ ብርሃን እና ፍጹም ሐሴት እንደደረሱ ሁሉ እኛም ዓላማችን ይህን መሰል ጉዞ አድርጎ እነሱ ከደረሱበት መድረስ ስለሆነ ነው ። ይህ ጉዞ አንዳንዶች ተለይተው የሚጓዙበት ሳይሆን የሁሉም ክርስቲያን ጉዞ ነው ። ኤማሁስም ከዚህ የተለየ ህላዌ የላትም ።

በኤማሁስ ጉዞ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢራት ተገለጡ ። በመጨረሻም ጉዞው በሥጋውና በደሙ ተደመደመ ። ይህም ሁሉ በራሱ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተደረገ ። በጥንታዊቷ ኤማሁስ የሆነው ይህ ሁሉ በዛሬዋም ኤማሁስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊሆን ይገባዋል ። ይሆናልም ። ኤማሁስ ፕሬስም ለዚህ ነገረ መለኮታዊ ተዋሥኦ መቀጠልና መዳበር ሲባል ወደ መኖር መጣች ።

ዓላማችን

ነገረ ሃይማኖት ከጠቅላላው ሕይወት የተለየ ሳይሆን የሕይወት መሠረት እና ምሰሶ እንደ መሆኑ ፣ ክርስቲያኖች ሁሉንም ነገር በነገረ ሃይማኖት መነጽር ካልሆነ በስተቀር ልንመለከተው አይገባንም ። ያን ማድረግ ከተገለጠልን እውነት መፋታት ይሆናልና ። አንድም ነገረ ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያን ቅጽሮች ውስጥ ወይም ነጠላ በሚለበስባቸው ዓውዶች የተገደበ ሳይሆን በእያንዳንዱ የሕይወታችን ቅጽበት ሐሳባችንን ሊመሠርት እና ሊመራ ይገባዋል ። ስለዚህም ኤማሁስ በዚህ መርሕ እና መረዳት መሠረት ፣ በአንድ በኩል ነገረ ሃይማታዊ የሆነን ተዋሥኦ ዘወትር በምንጠቀምባቸው መድረኮች እና ዓውዶች በኩል ፣ ዘወትር በምንነጋገርበት መንገድ የማቅረብ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተዋሥኦው “ሃይማኖታዊ” በሚባሉ ርእሶች ሳይገደብ ወደ ሁሉም የሕይወታችን ክፍሎች እንዲሰፋ ፣ በተለይም በዘመናችን ያጋጠሙንን ፈተናዎች ፣ ዕድሎች ፣ ጥያቄዎች ወዘተርፈ የጠቀለለ እና የዳበረ እንዲሆን የማድረግ ተልዕኮ አላት።

ዳግመኛም በዘመናችን በሚደረጉት ሕዝባዊ ተዋሥኦዎች ውስጥ በእጅጉ የሚስተዋለውን ሸቃጭነት ፣ ጭፍን ወገንተኝነት ፣ ከቁም ነገር መቅጠን እና ጥራዝ ነጠቅነት በመሸሽ ፣ የታሰበበት ፣ ዝግጅት እና ንባብ የተደረገበት ፣ ጥልቀት ያለው እና ከሕይወት ጋር ቁርኝት ያለው አቅርቦት የማድረግ ዓላማ አላት ። ሕዝባዊ ተዋሥኦውንም በዚህ አቅጣጫ ለመግፋት በሚያስፈልገው መጠን ተጠየቅን ትፈጥራለች ። እንደምትጠይቀው ደግሞ መጠየቅንም ትወድዳችለች ።

በጠቅላላው ኤማሁስ ከቤተ ክርስቲያን የተነጠለ ግብ የላትም ። ክርስቲያኖችን ማጽናት ፣ ሕዝባውያንን ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥራት ። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሁሉም የራሱ ልዩ ሚና አለውና ኤማሁስም የራሴ ብላ ከያዘችው ሚናዋ አንጻር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውነትን መሠረት ያደረገ እና ዘመኑን የዋጀ – በዘመናችን ካጋጠመን ሁለንተናዊ ድቀት ለመውጣት መነሻ የሚሆን ተዋሥኦ መፍጠርን ትሻለች ። እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ካሉ ሕዝባውያን ጋር እነርሱን ወደ ኅብረቱ መጥራትን ዓላማው ያደረገ እንጂ መበሻሸቅ ያልሆነ ፣ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በነቢብም በገቢርም በሚገባ የሚወክል ተዋሥኦ እንዲፈጠር ትሻለች ። ስለዚህ በተለያዩ አቅርቦቶቿ አጋፋሪዎቿ እና ታዳሚዎቿ ስለ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና ትውፊት የዳበረ መረዳት ይኖራቸው ዘንድ ፣ በተለይም ደግሞ በሴኪዩላሪዝም ጦስ ያጣነውን ኦርቶዶክሳዊ ርእዮት ፣ ማለትም ነገረ ሃይማኖትን ዐይናችን ማድረግን ፣ ገንዘብ ለማድረግ እንደ ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች ጉዞ እንዲጀምሩ እንመኛለን ። ወደ ኤማሁስ ጉዞ ከተጀመረ ዐይነ ልቡና ሰጪው አብሮ መጓዙ አይቀርምና ።

ግባችን

ለነገረ ሃይማኖት ንባብና ዕውቀት የበረቱ እና በንባብ እና በዕውቀታቸው ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ምስጢር የሚገቡ ፣ ከዚህ ጉዟቸው ያገኙት ብርሃን ደግሞ ከእንቅብ በታች የተሸፈነ ሳይሆን በአደባባይ የሚበራ ተዋሣእያን በክርስቲያኑ ኅብረት ውስጥ መፈጠሩ የኤማሁስ ተስፋዋ ነው ።

በኤማሁስ ቤት

ውይይቶች

የጥያቄዎች መልስ

መጣጥፍ

ከእንግዳ ጋር ቆይታ