መግቢያ
በዘመናችን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታየው “የአእላፋት ዝማሬ” የተባለው ክሥተት ሰፊ የሆነ ሕዝባዊና ሊቱርጊያዊ ውይይት አስነስቷል። አንዳንዶች ይህን እንቅስቃሴ እንደ መንፈሳዊ ንቃትና የራቁ ምእመናን ተሳትፎ መመለሻ ሲያቀርቡት፣ ሌሎች ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሊቱርጊያ[1] ጋር የሚጋጭ እና ሥርዓታዊ መነሻዋን የሚያዳክም ክዋኔ እንደሆነ ይገምግሙታል። ወንድማችን በርናባስ ሽፈራው የጻፈው “የአእላፋት ዝማሬ”ን የተመለከተ የኤማሁስ ገጽ ጽሑፍ አንዳንዶችን ሲያበሳጭ፣ ሌሎችን ሲያሳስብ እንደሰነበተ በአረቦን ቴሌግራም ቻነል ላይ ተመልክቻለኹ። 23 ገጾችን የያዘ፣ ንዑሳን አርእስት በግልጽ ያልተሰጡት ረዥም ጽሑፍ ስለኾነ ጊዜ ሰጥቶ ማንበብን፣ ካነበቡም በኋላ ዐበይት መከራከሪያዎቹን ማጥለልን ይጠይቃል። እንዲኽም ኾኖ፣ ቢያንስ መሠረታዊ የኾነ የሊቱርጊያዊ ነገረ መለኮት (liturgical theology) ንባብ ለሌለው ሰው ጽሑፉ ከንቱ ምቀኝነት፣ መራራነት፣ አማራሪነት፣ ጠብ ያለሽ በዳቦ ሊመስል ይችላል። በዋናነት እየነቀሰ የሚተቸው “የአእላፋት ዝማሬ”ን ልዩ ልዩ መልኮች ይኹን እንጂ፣ መሠረታዊ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ጊዜ ያለችበትን ሊቱርጊያዊ ቀውስ (liturgical crisis) መጠቆም ኾኖ አግኝቼዋለኹ። ጉዳዩ እኔንም ሲያሳስበኝ የነበረ ነገር ስለነበረ የበርናባስን ሐሳብ እንዲኽ ልለጥቀው ወደድኹ። የእኔ ጽሑፍ የ“የአእላፋት ዝማሬ”ን እንደ ምልክት በመመልከት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ የምትገኝበትን ሊቱርጊያዊ ቀውስ ይጠቁማል። በተለይም በቋንቋ ባዕድነት፣ በዜማ ውስብስብነትና በሰዓት ምቹ አለመኾን ምክንያት ምእመናን ከ“ሰዓታት ጸሎት” የራቁበትን ኹኔታና ኮንሰርታዊ ዝግጅቶች በተግባር የተኩት የሊቱርጊያ ባዶ (liturgical vacuum) ምን እንደሆነ ለማመልከትና መፍትሔውን ለማሳየት ይጥራል።
The Problem of Reactive Ministry እና Institutional Survivalism
በርናባስ በጽሑፉ የሚተቸው አንዱ ነገር ይኽ ተልእኮን ሳይኾን ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮረውን የአገልግሎት ቅኝት (minsterial orientation) ነው። የአእላፋት ዝማሬ በሊቱርጊያ ሱታፌ የተነፈጉ ምእመናን የፈጠሩት እንቅስቃሴ ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በ20ኛው ክፍለ ዘመን የገባችበትን ተግዳሮት ለመወጣት የሞከረችበት መንገድ እየተስፋፋ ከመጣው ከተሜነትና ዘመነኛው ትምህርት ጋር የሚጣጣም አልነበረም። ከተሞችን የገቢ ምንጭና የቤተ ክህነታዊ ፖለቲካ ኃይል ሚዛን ማዕከላት ከማድረግ የዘለለ ከተሜውንና በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ እየተቃኘ የሚያድገውን ትውልድ በሊቱርጊያ የሚያሳትፍ አልነበረም። ምእመኑ ይመጣል፤ ይሳለማል፤ ይኼዳል። በርናባስ ከመርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ መጽሐፍ የጠቀሳቸው እንደ አባ ኪዳነ ማርያም ባሉ ጥቂት አባቶች ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች ከግለሰባዊ ጥረትነት አላለፉም። ጥረቶቹ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲያገኙ ለማድረግ የተደረገበት ዋና ሙከራ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አደረጃጀት ነው። እርሱም ቢኾን ግን ወጣቶችን ሰብስቦ መሠረታዊ ነገረ ሃይማኖት ከማስተማርና መዝሙር ከማስዘመር ባለፈ ግብረ አምልኮን ማዕከል ያደረገ አልነበረም። የነገረ ቤተ ክርስቲያን እሳቤውም የቅዱስ ቍርባን ጉባኤነቷና ወደ ዓለም ይዛ በምትኼደው ቍርባናዊ ተልእኮ ላይ አይደለም። ይልቁንም ከብሔራዊ ተቋምነቷ ላይ የሚጀምርና ተቋሟ ለቀጣዩ ትውልድ እንድትደርስ የማድረግ የህልውና ትግል ላይ የሚያተኩር “እንዳንጠፋ!” ባይ እሳቤ (institutional survivalism) ነው።[2]
በተለይ የፕሮቴስታንቲዝም እንቅስቃሴ እየበረታ ሲመጣና ከተሜውንና ዘመነኛ ትምህርት የቀማመሰውን በቀላሉ ጠቅልሎ ሲወስደው ያዩ ቀናዕያን ፕሮቴስታንቲዝምን ለመገዳደር ስብከትና መዝሙር ላይ ያተኮረ አገልግሎት አበጁ። አገልግሎቱ በተለይ ከ1983 ወዲኽ በነበረው ዘመን ግለሰባዊ መዝሙሮች በረከቱበት። የኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ዐቢይ መለኪያው ይዘት ሳይኾን የዜማ መሣሪያዎች ዓይነት እስኪመስል ድረስ ነገረ መለኮታዊ ችግር ያለባቸው፣ ስሜታዊነት ያየለባቸው፣ ማዕከላዊና ዳርቻዊ ጉዳዮችን፣ የግል ጸሎትና የአደባባይ ተዋሥዖ የማይለዩ፣ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የታጀቡ መዝሙሮች በገበያው ላይ በብዛት ተመረቱ።[3] የቋንቋቸው ታዋቂነት፣ የዜማቸው ቀላልነትና ተመሳሳይነት መዝሙሮቹን ተወዳጅ አደረጋቸው። ከፕሮቴስታንቲዝም ጋር በነበረው ትንቅንቅ የዐውደ ምሕረት የሰርክ ጉባኤ[4] አገልግሎት ሲገንን እነዚኽ መዝሙሮች አብረው ገነኑ።
በሕዝባዊው ተዋሥዖ (popular discourse) ጾሙ “የቄስ” እንደኾነ የተነገረው፣ ማኅሌቱ “የሊቃውንት” እንደኾነ የሰማው፣ ደብሩ “የአባቶች” እንደኾነ የተሰበከለት ምእመን አንድ እርሱ በንቃት፣ በትጋት፣ በደስታ ሊሳተፍበት የሚችል ነገር አገኘ። ቋንቋውን ያውቀዋል፤ ዜማውን በቀላሉ ይከተለዋል፤ ከቢጤዎቹ ጋር በአንድነት ያመሠግንበታል። በዚኽ አገልግሎት ለመሳተፍ እንደ ቅዳሴ ከጠዋቱ በ10፡00 ሰዓት ከዕንቅልፉ መነሣት አይጠበቅበትም። እንደ ማኅሌት ግእዝ የሚባል ቋንቋ መማርና ውስብስብ ዜማ ለዓመታት ወይም ለሰዓታት ማጥናት አይጠበቅበትም። ዝግጅቱም ከሥራው ውሎ ሲመለስ አመሻሽ ላይ በድምፅ ማጉያ ታጅቦ ይጠብቀዋል። ትምህርት ተብሎ የሚቀርብለትን ሰምቶ፣ ጧፍ አብርቶ፣ ብርዱን ታግሦ፣ አብረውት ከተሰበሰቡት ወንድም እኅቶቹ ጋር ዘምሮ ከኹለት ሰዓት ተኩል ባልበለጠ ጊዜ ወደ ቤቱ ይገባል።[5] ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በዜማው ከባድነት፣ በቋንቋው ባዕድነት በአምልኮ ረኀብ ሲሰቃይ የነበረው ሰው አኹን ጎደሎውን የሞላለት የመሰለው ነገር አገኘ።
እንዲኽ ያለው ሊቱርጊያን የመተካት እንቅስቃሴ በክርስትና ታሪክ በተደጋጋሚ ይታያል። ሰዎች ለማምለክ የተፈጠሩ ስለኾነ ግብረ አምልኮን ይሻሉ። በሊቱርጊያዊ ባዶ (liturgical vaccuum) ውስጥ መኖር አይችሉም። ክርስቲያኖች ሊቱርጊያው ሲጽንንባቸው ወይ ሊቱርጊያውን የሚተካላቸው ሐሳዊ-ምትክ (pseudo-substitute) ይፈጥራሉ፤ አልያም እርግፍ አድርገው ይተዉታል።[6] ለምሳሌ፣ በመካከለኛው ዘመን የላቲን ክርስትና ሰዉ ቅዳሴው አልገባውና አላሳትፈው ሲል ቅዳሴ እየተቀደሰ የመቁጠሪያ ጸሎት ይደግም ነበረ። በግሪኮችና በስላቮች ዘንድም በቋንቋ ባዕድነትና በዜማ ውስብስብነት የሊቱርጊያ ሱታፌ የተነፈጉ ምእመናን የሚመጡት ቅዳሴው ሊያልቅ ሲል ነበረ።[7] በእኛም ዘንድ በገጠር አካባቢ “ሴት ተሰጥዖ አትቀበልም” የሚል ልማድ እንዳለ ይታወቃል። ወንዶቹም ቢኾኑ ቍርባንና ቅዳሴ የሕጻናትና የአረጋውያን እንጂ የጎልማሶች ነው ብለው ስለማያስቡ ቤተ ክርስቲያን ድርሽ አይሉም። ከመጡም ከቅዳሴ ውጪ የቤተ ክርስቲያኑን ደጃፍ ስሞ የግል ጸሎት አድርሶ ለመኼድ ነው። ልጆቻቸውን ማቁረብ የሚፈልጉ እናቶች ቅዳሴ ሊያልቅ ሲል ጨቅሎቻቸውን አንጠልጥለው እየተጣደፉ ይደርሳሉ። እነርሱ አይቆርቡም፤ ልጆቻቸውን ግን “ለጤንነታቸው” ጥሩ እንደኾነ ስለሚያምኑ ያቆርባሉ።[8]
ከአራተኛው ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቤተ ክርስቲያንን በፍጥነት እንድትስፋፋና ምእመናንም በክርስቶሳዊ ሕይወታቸው ብርታት እንዲኖራቸው ካደረጉ ነገሮች መካከል የሊቱርጊያዋ ውስብስብ አለመኾንና ኹሉን አሳታፊነት ነበረ። ያለ ምእመናን ምሉዕ ሱታፌ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ፈጸመች ሊባል አይችልም። በሲኖዶስና በፍትሐ ነገሥት ውስጥ የምናገኘው ሥርዓተ ቅዳሴ ግልጽ፣ ቀጥተኛና ድግግሞሽና ድጋም የሌለበት መኾኑን ማስተዋልም ይጠቅማል። ፍትሐ ነገሥትም “ኢውጥኑ ቅዳሴ ዘእንበለ ይትጋብኡ ኵሉ ሕዝብ” (ሕዝቡ ኹሉ ሳይሰበሰቡ የቅዳሴውን ጸሎት አይጀምሩ!) ያለው ያለምክንያት አይደለም። የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ የእነዚኽ አማኞች ጸሎትና መሥዋዕት፣ የእነርሱ ሥራ ስለኾነ ነው። ዜማውም፣ ሰዓቱም፣ ዝግጅቱም ለእነርሱ የተስማማ መኾን አለበት።
የዮስጢኖስ ሰማዕት፣ ሂፖሊተስ ዘሮም፣ የዲዳኬ ምስክርነቶች ኹሉ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ ምን ያኽል ቀላል፣ ቅልጥፍ ያለና ምእመናን ኹሉ የሚሳተፉበት እንደነበረ ይመሰክራሉ።[9] ቋንቋው፣ ዜማው፣ ክንውኑ ውስብስ፣ በቀላሉ ለመከተል አስቸጋሪና ለባለሙያዎች የተተወ አልነበረም። መዘምራን ሕዝቡን እንዲዘምር ይመሩታል እንጂ ሕዝቡን ተክተው አይዘምሩም። ቅዱስ ኤፍሬም ሴት መዘምራንን ሲያደራጅ መዘምራኑ ሕዝቡን በዝማሬ እንዲመሩትና እንዲያስተምሩት እንጂ እነርሱ ሕዝቡ በማይገባው ቋንቋ እየዘመሩ ሕዝቡ አፉን በእጁ ጭኖ አጀብ አጀብ እያለ ታዛቢ እንዲኾን አልነበረም።[10] እነርሱ ይመሩታል። ሕዝቡም ዝማሬያቸውን በንቃት ያዳምጣል፤ ተከትሏቸው ይዘምራል።[11]
A Friendly takeover
በንግድ ዓለም አንድ ኩባንያ ሌላን ኩባንያ በጉልበት አስገድዶ ሲገዛውና የራሱ ሲያደርገው “hostile takeover” ይባላል።[12] የአእላፋት ዝማሬ አዘጋጆች የቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለኾኑ እውነተኛ ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያንን መተካት ወይም መገዳደር እንዳልኾነ ማመን አያስቸግረኝም። ስለዚኽም፣ እየኾነ ያለው ነገር “hostile takeover” አይደለም ብዬ አምናለኹ። ይኹን እንጂ፣ በርናባስም በበቂ ኹኔታ እንዳቀረበው አዘጋጆቹ በቅን ሐሳብ የፈጠሩት ወይም ከሰርክ ጸሎት ከተፋቱ “የሰርክ ጉባኤዎች”፣ ከ”ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብሮች” እና ከተሞካከሩ “የሚሌኒየም አዳራሽ የመዝሙር ኮንሰርቶች”፣ ወዘተ. ወስደውና ኮንሰርታዊ ደረጃውንና ኮሪዮግራፊውን በጣም አሻሽለው ያቀረቡት ነገር በግልጽ የቤተ ክርስቲያንን ሊቱርጊያ የሚተካ ነገር ነው። ስለዚኽ፣ እነርሱ ዐውቀው ባያደርጉትም ነገሩ በምእመናን የተመራ “Friendly takeover” ሊባል የሚችል ይመስለኛል።
በተቋማዊ የእኖር ባይነት እሳቤ የተያዙት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጉዳዩን ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የመፍጠሪያ፣ ሕዝባዊ ዐቅምን የማሳያ፣ ጎልቶ ደምቆ የመታያ አድርገው ቢመለከቱትና ቢያበረታቱትም ሕዝቡ ግን በዋናነት የሚመጣውና ለሰዓታት ቆሞ የሚዘምረው ፖለቲካዊ አጀንዳ ይዞ ሳይኾን ተሰብስቦ መዘመር ስለሚፈልግ ነው፤ የሰው ልጅ “homo adorans” (አምላኪ ፍጡር) ነው እንዲሉ።[13] ስለዚኽ፣ የአእላፋት ዝማሬም ኾነ ሌሎች ኮንሰርታዊ ዝግጅቶች ምእመናንና ለውስብስቡ የዜማ ትምህርት ጊዜ ያልነበራቸው ቅን ካህናት ሳያስቡት በባለሙያ ደባትር” (professional singers) የተነጠቁትን የሊቱርጊያ ዘርፍ በተግባር ሊያስመልሱና ሊቱርጊያውን በድጋሚ ሕዝባዊ ለማድረግ የሞከሩበት እንቅስቃሴ አድርጌ እመለከተዋለኹ።
የአእላፋት ዝማሬ በውስጡ ተግባራዊ ምላሽ የሚፈልግ የምእመናን ጥያቄ አዝሏል። “የአእላፋት ዝማሬ ይቅር በቃ!” ብሎ መከልከል መፍትሔ የሚኾን አይመስለኝም። ዛሬ የአእላፋት ዝማሬን ብንከለክል ጥያቄውን እስካልመለስን ድረስ ሌላ የአእላፋት ዝማሬ “ደረጃውን በጠበቀና ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትን በተከተለ መልኩ” ተብሎ መምጣቱ አይቀርም። የአእላፋት ዝማሬ ላለንበት ሊቱርጊያዊ ቀውስ ምልክት እንጂ ችግሩ ራሱ አይደለም። ስለዚኽ የአእላፋት ዝማሬ የሚያመለክተውን ችግር በጥንቃቄ ማጤን አለብን። ማለትም የአእላፋት ዝማሬ የትኛውን የሊቱርጊያ ክፍል እንደተካ ማስተዋል የሚያስፈልገን ይመስለኛል። ለዚኽም “የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ መደበኛ ክፍሎቹ እነማን ናቸው?” የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።
የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ ኹለት ዋና ዋና ዘርፎች አሉት። አንደኛው የሰዓታት ጸሎት ነው። ኹለተኛው ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ማዕከል የኾነው ቅዱስ ቍርባን ቅዳሴ ነው።[14] እንደእኔ ሐሳብ፣ የአእላፋት ዝማሬም ኾነ ሌሎች ኮንሰርታዊ ዝግጅቶች የተኩት በቋንቋ ባዕድነት፣ በዜማ ውስብስብነትና በሰዓት ምቹ አለመኾን ምእመናን የተነፈጉትን የሰዓታት ጸሎት (liturgy of hours) ነው። ዛሬ ሰዓታት ሲባል አብዛኛው ሰው የሚያስበው ሌሊት የሚቆመውን ጸሎት ብቻ ስለኾነ ጉዳዩን ጥቂት ማብራራት ያለብኝ ይመስለኛል።
የሰዓታት ጸሎት ምድነው?
የሰዓታት ጸሎት ከጥንት ከአይሁድ እምነት ጀምሮ ነበረ። አማኞች ሰዓቱን ለእግዚአብሔር የሚቀድሱበት ወደ እግዚአብሔር ጸሎት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነው። በመደበኛነት ሰባት የታወቁ የጸሎት ጊዜዎች አሉት። ከእነዚያ ጊዜያት በተጨማሪ የሚጸልዩ ማኅበራትና ክርስቲያኖች መኖራቸው ግን እሙን ነው።[15] ይኽም፣ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” (1 ተሰሎ 5፡ 16 ) የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ትእዛዝ በመከተል በዓለም ዙሪያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ቀን ከሌሊት ምሥጋና፣ ጸሎትና ምልጃ አይቋረጥባትም ያሰኛል። እንደ ቅዳሴው ኹሉ የሰዓታት ጸሎት ተሳታፊዎችም ምእመናን በሙሉ ናቸው። ምእመናን በሚያውቁት፣ በሚረዱት፣ በሚናገሩት ቋንቋ ሊኾን ይገባል። የሰዓታት ጸሎት ዋና ይዘቶቹም መዝሙረ ዳዊት እና የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባብ ናቸው።[16] የቀደመው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ጸሎትም ይኽንን የሚከተል ነበረ። ለዚኽም ቀደም ያሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብራናዎችን ጭምር መመልከት ይቻላል።[17] ሰዓታት ኹለት ዓይነት መልኮች አሉት። አንደኛው የገዳማት ሰዓታት ነው፤ ኹለተኛው ደግሞ የካቴድራል ሰዓታት ይባላል። ኹለቱም ዋና ይዘታቸው መዝሙረ ዳዊት፣ የምልጃ ጸሎት፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባብ ናቸው። ነገር ግን፣ የካቴድራል ሰዓታት ከገዳም ሰዓታት የበለጠ የሚታጀብበት የዜማ ይትበሃል አለው።[18]
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የካቴድራል ሰዓታት በተለምዶ ማኅሌት እየተባለ የሚጠራው በመዘምራን የሚከናወነው አገልግሎት ነው። አኹን ባለው ኹኔታ ሥርዓተ ማኅሌት የሰዓታት ጸሎት አንዱ መልክ እንደኾነ ተዘንግቷል ቢባል ድፍረት አይኾንም።[19] ከግእዝ ቋንቋ አለመታወቅና ከዜማው ከባድነት የተነሣ ምእመናን አይረዱትም፤ በስሜት ከማጨብጨብና ዕልል ከማለት በዘለለ በባለቤትነትና በማስተዋል የሚዘምሩበት ዕድላቸው በጣም አናሳ ነው። እንኳን ምእመናን አብዛኞቹ ካህናት እንኳ በዚኽ ሥርዓት ለመሳተፍ ያዳግታቸዋል። ስለዚኽም፣ ይኽ ጸሎት መላዋን ቤተክርስቲያን በተመልካችነት ትቶ ልዩ ሥልጠና የወሰዱ መዘምራን ብቻ የሚከውኑት፣ ከሌላው የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ ጋር ያለው ትሥሥር የማይታይበት እንግዳ ቅርስ ኾኗል። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለበዓል የሚሰበሰቡ ምእመናን ማኅሌት በሚቆምበት ጊዜ ሰብሰብ ብለው ከውጪ፣ ብርድ እየለበለባቸው የራሳቸውን ባህላዊ ዝማሬ የሚያከናውኑት ሥርዓተ ማኅሌቱ ለእነርሱ ሊሳተፉበት የማይችሉ ባዕድ ስለሚኾንባቸው ነው። በንግሥ ቀን ለማዕጠንት በምንዞርበት ጊዜ በመንገዳችን ላይ ቆንጆ ዜማ እያዳመጡ የተኙትን ሰዎች መቀስቀስ የብዙ ዲያቆናት የተለመደ ገጠመኝ ይመስለኛል። ለማምለክ የመጣው ሰው የሚያስመልከው ሰዓታት ሲያጣ ቆንጆ ዜማ እየሰማ ይተኛል። ምን ያድርግ?
በምእመናን ተሳትፎ ረገድ ጥቂት የተሻለ ኾኖ የሚታየው በተለምዶ “ሰዓታት” ሲባል የሚታሰበው የአባ ጊዮርጊስ ሰግላዊ ድርሰቶች ላይ የተመሠረተው “ሰዓታት ዘሌሊት” ነው። ይኽ አሁን ያለው የሌሊት ሰዓታት ምንም እንኳ የአባ ጊዮርጊስን ድርሰቶች ቢይዝም መቼ እንደተጨመሩ እንኳ በቅጡ የማይታወቁ ብዙ የሚዜሙ ድርሰቶች አሉት። በእነዚኽ በኋላ ዘመን የተጨማመሩ የሚዜሙ ብዙ ድርሰቶች ምክንያትም አባ ጊዮርጊስ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ሰዓታት በመከተል ለየሰዓቱ የመደቧቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ኹኔታ አይነበቡም። ምንባባቱ በታተሙ የሰዓታት መጻሕፍት ውስጥ እንኳ ሲካተቱ አይታይም። በተጨማሪም፣ ጊዜ ለማብቃቃት እየተባለ ዜማው እንኳ በቅጡና ለአምልኮ በሚመጥን መልኩ ሲዜም አይስተዋልም። ኹሉን ከማዜም የተወሰኑትን ብቻ መርጦ በማዜም ሌላውን በሰከነ መልኩ በንባብ እየተቀባበሉ ተረጋግቶ መጸለይ አማራጭ ተደርጎ ሲወሰድም አይታይም። በዐጭሩ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ በመላዋ ቤተ ክርስቲያን የማይከናወን፣ የተወሰኑ “ባለሙያዎች የሚያደርሱት”፣ እንደሥራ “ለባለሙያዎች” የተተወ ነገር ኾኗል ቢባል ማጋነን አይኾንም።
ይኽ ምንም እንኳ እኛ ስለለመድነው ትክክል መስሎ ቢታየንም ፍጹም የኦርቶዶክሳዊ ክርስትና ትውፊት አይደለም። ሐዋርያትም፣ ሐዋርያውያን አበውም፣ የቀደሙ ሊቃውንትም እንዲኽ ያለ ወለፈንዴነት አላወረሱንም። ለምሳሌ፣ መጽሐፈ ሲኖዶስ የተሰኘው የቀደሙ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎች ስብስብ ምእመናን በየስንት ሰዓቱ መጸለይ እንደሚገባቸው ይደነግጋል። በአሥራ ኹለተኛው ክፍለ ዘመን የተቀናበረውና በአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ግእዝ የተተረጎመው “ፍትሐ ነገሥት” የተሰኘው የቀኖናዎች ስብስብም ምእመናን ኹሉ በሰዓታት ጸሎት መሳተፍ እንዳለባቸው ሲያሳይ እንዲኽ ይላል፦
ወጸሎትሰ ዘተአዘዘ ላዕለ ኵሎሙ ምእመናን በኵሉ ዕለት ፯ቱ ጊዜያት። … ወለእመቦ ኮነ ምስለ ብእሲቱ ፪ሆሙ ይጸልዩ ኅቡረ። … ወይኩን ጸሎተ ነግህ ወሰርክ ውስተ ቤተ ክርስቲያን።[20]
(ዘወትር ለምእመናን ኹሉ የታዘዘው ጸሎት ግን በ፯ቱ ጊዜያት ነው። … ከሚስቱ ጋር ቢኾን ኹለቱም በአንድነት ይጸልዩ። … የጠዋትና የሰርክ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኹን።)
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአቋቋም ዜማ ክብደትና ውስብስብነት ውበቱና ቅርስነቱ ታላቅ ቢኾንም የምእመናን ሱታፌ ከሰዓታት ጸሎት እንዲርቅ፣ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያ ባዕድ እንዲኾኑ ምክንያት መኾኑን ግን መካድ አይቻልም። በሊቱርጊያ የማይሳተፉ ምእመናን ደግሞ የጸሎት ሕይወታቸው ይላሽቃል። ጠንካራ የቤተ ክርስቲያን ማንነትም አይኖራቸውም። ማንነታቸውን ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ በወደቀው ዓለም ሥርዓትና ፍልስፍና እንዲበይኑት ያደርጋቸዋል። ስለዚኽ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሊቱርጊያ መነቃቃት ያስፈልጋል። ቤተ ክርስቲያን አማናዊ ማንነቷን መኖር፣ መዳኗን መፈጸምና ዓለሙንም ማዳን የምትችለው እንዲኽ ባለ ጠንካራ የማይቋረጥ የጸሎት ሕይወት ውስጥ የምትኖር ከኾነ ብቻ ነው።
እና የአእላፋት ዝማሬ ምን ይኹን?
የአእላፋት ዝማሬን በተመለከተ ኹለት አማራጮች አሉን። አንደኛው የአእላፋት ዝማሬን የቤተ ክርስቲያን የልደት ዝግጅት የሰዓታት ጸሎት ነው ብለን በዐዋጅ መቀበል ነው። የላይ ቤት የታች ቤት፣ የጎንደር፣ የአጫብር እንደሚባለው፣ ይኽንንም የከተሜዎች ወይም የጭቁኖች፣ የዜማ ቢሶች ሰዓታት፣ ወዘተ. ብለን ማወጅ እንችላለን። ይኹን እንጂ፣ የአእላፋት ዝማሬን አኹን ባለበት መልኩ በሰዓታትነት መቀበል ሐዋርያዊውን ትውፊት መጣል ይኾናል። ዝግጅቱ ግለሰባዊ መዝሙሮች የሚዘመሩበት ስለኾነ በኦርቶዶክሳዊ ሊቱርጊያዊ ትውፊትና በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሲሰፈር ተቀባይነት አይኖረውም።
ኹለተኛው አማራጭ፣ የአእላፋት ዝማሬን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላለችበት ሊቱርጊያዊ ቀውስ ምልክት አድርጎ ማየት ነው። የሰዓታት ጸሎት በቋንቋ ባዕድነት፣ በዜማ ውስብስብነት፣ የምእመናንን ኑሮ ከግምት ባላስገባ የሰዓት መርሐ ግብር ምክንያት ምእመናንን ሲያገልል ምእመናን የራሳቸውን ሌላ ምትክ ለመፍጠር መሞከራቸው አይቀርም። ተሰብስቦ ማዜም የሰውን ልጅ እጅግ ከሚያስደስቱት ነገሮች አንዱ ነው። እንደ የአእላፋት ዝማሬ ያሉ ኮንሰርታዊ ዝግጅቶች የዚኽ ምልክት ናቸው። እነዚኽን የሊቱርጊያዊ ሕመማችን ምልክቶች ህልውናቸውን “የሉም” ብለን በመካድ ወይም ዜማና ልብስ በማሻሻል ኦርቶዶክሳዊነትን መጠበቅ አንችልም። ማድረግ የሚገባን የሰዓታት ጸሎትን ከነጥንታዊ የመዝሙረ ዳዊትና የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባቱ እንዲኹም ከቀላል አሳታፊ ዜማዎቹ ጋር ወደ ቦታው መመለስ ነው። በዚኽም ምእመናን በሊቱርጊያቸው በእውነት፣ በንቃት እንዲሳተፉ እናደርጋለን። ክዋኔውም ሕዝቡን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ነቅሎ ሌላ ቦታ የሚወስድ ሳይኾን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ መኾን ይኖርበታል። በዚህም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ከባዶ ግንብነት አልፈው ጠንካራ የምእመናን የዘወትር ጸሎት ስፍራ ይኾናሉ። ጥገኛ፣ ትይዩና ተገዳዳሪ የኾኑ ገበያ ተኮር አደረጃጀቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳናራባ የተቀደሰውንም በገበያዊ አስተሳሰብ እንዳንሸቃቅጥ ይጠብቀናል። በጠቅላላው፣ ኦርቶዶክሳዊውን ሕዝብ በኦርቶዶክሳዊው የአባቶቹ ሊቱርጊያ ይተክለዋል።
[1] ሊቱርጊያ (λειτουργία) የግሪክ ቃል ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ “የሕዝብ ሥራ” ማለት ነው ። ይህ ቃል በመጀመሪያው የክርስትና ዘመን ክርስቲያኖች ተሰብስበው የሚፈጽሙትን አምልኮ ለመግለጥ ጥቅም ላይ ውሏል ። በነገረ ሃይማኖት ውስጥ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙትን አምልኮ በጥቅሉ ይገልጣል ።
[2] የመጋቤ ሐዲስ እሸቱ መልስ ለዚኽ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል። “በዋሽንግተን ፖስት፣ በሲኤን ኤን፣ በአልጀዚራ መታየት፣” “ዓለም ዐቀፍ ብራንድ” መኾን፣ ገበያ ማሟሟቅ ወዘተ. ከተቋማዊ እኖር ባይነት ቅኝት የሚመጣ ነው። ተቋማዊ እኖር ባይነት አንዱ የሚታወቅበት መልክ በሌሎች ዘንድ መታየት፣ መታወቅ፣ መወደስ መፈለግ ነው።
[3] ይኽን የዘመናችንን ጣጣ ከሎዶቅያ ጉባኤ (363-64) ሐምሳ ዘጠነኛው ቀኖና አኳያ ሳየው የጥንቶቹ የግል ዝማሬ የሚባል ነገርን የሸሹበትን ምክንያት የበለጠ እንድረዳው ያደርገኛል። ቀኖናው እንዲኽ ይላል፦ Ὅτι οὐ δεῖ ἰδιωτικοὺς ψαλμοὺς λέγεσθαι ἐν τῇ ἐκκλησίᾳ, οὐδὲ ἀκανόνιστα βιβλία, ἀλλὰ μόνα τὰ κανονικὰ τῆς Παλαιᾶς καὶ Καινῆς Διαθήκης. “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የግል መዝሙርና ቀኖናዊ ያልኾኑ መጻሕፍትን አይነበቡም፤ ቀኖናዊ ከኾኑ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንጂ።” The Canons of the Synod Held in the City of Laodicea, in Phrygia Pacatiana (363 AD), https://patristica.net/laodicea&g&e&r&c.
[4] የሰርክ ጉባኤ አገልግሎት ሥሪቱ የቤተ ክርስቲያንን የሰዓታት ጸሎት ቅጥ ለመከተል የሚሞክር ነበረ። የዘወትር ጸሎት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ የወንጌል ንባብ የሥሪቱ አካላት ነበሩ። የወንጌል ትምህርቱም የሚሰጠው እንዲያው ሰባኪው ያሻውን ሳይኾን ከወንጌል ንባቡ ላይ መሠረት ያደረገ እንዲኾን የተዘጋጀ ነበረ። ፕሮቴስታንቲዝምን ለመቃወም የተደረገው ትንቅንቅ ስብከቱ ላይ ሲያተኩር የሰርክ ጸሎት መኾኑ ቀረና የሰርክ ስብከት ጉባኤ ኾነ። መለኪያ ሚዛኑም የስብከቱ ጩኸትና የዘማርያኑ መዝሙር ኾነ።
[5] ሰው በተፈጥሮው ተሰብስቦ ማዜም ይወድዳል፤ ኅብራዊ ዜማም እንደ ኢንዶፍሪንና ሴሮቶኒን ያሉ የደስታ ሆርሞኖቹን ያነቃቃቸዋል Tarr B et al., “Music and Social Bonding: ‘Self-Other’ Merging and Neurohormonal Mechanisms.,” Frontiers in Psychology 5, no. 1096 (2014), https://doi.org/doi:%252010.3389/fpsyg.2014.01096; Frontiers, “Melody Modulates Choir Members’ Heart Rate,” Science Daily, n.d., www.sciencedaily.com/releases/2013/07/130708200153.htm (accessed December 31, 2025).
[6] በእንተ ቅዳሴ፣ አንቀጽ 12፡ 481 “ኢያዕርጉ ቍርባነ እንበለ ቍርባነ ምእመናን ወኢይትወከፉ መባኦሙ ለጸራፍያን ወለቀታልያን ወዘማውያን ወመጠዓውያን ወሰራቅያን ወገባርያነ ጣዖታት ወሰካርያን ወለእለ ያጽዕቁ ላዕለ ዕቤራት ወእጓለ ማውታ ወመጸብሐን ወሀያድያን ወዓማፅያን። ወእምነ ሐራ እለ የሀውኩ ነዳያነ ወእለ ይሞቅሕዎሙ ለሰብእ በዓመፃ ወእለ ይቀንዩ አግብርቲሆሙ ቅንየተ እኩየ ወእለ የሐሥሙ ላዕሌሆሙ ወእለ ይዔምፁ በግፍዕ ወነጋድያን እለ ይሠይጡ ቶሲሖሙ ማየ በወይን። ወኩሎሙ ዐላውያነ ሕግ እስመ እግዚአብሔር ይሜንን መሥዋዕተ ረሲዓን በከመ ይቤ ሰሎሞን ጠቢብ። ኢትሢጥ ብኩርናከ ኦ ካህን በተመጥዎተ ምንትኒ እምዘውእቱ ህልው ላዕለ ዕልወቱ።” (በእንተ ቍርባን፣ አንቀጽ 13፣ 501)። ይኽ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ሲታሰብ የሚቆጠሩት ምእመናን የትኞቹ እንደኾኑ በግልጽ ያሳያል። የቤተ ክርስቲያን ሊቱርጊያም የእነዚኽ አማኞች ጸሎትና መሥዋዕት ነው። የማይቆርብ ምእመን፣ የማይጸልይ ምእመን ከቤተ ክርስቲያን የፈለገ ወፍራም ማዕተብ ቢያደርግ ወይም የንግሥ ዝማሬ ሲያወርድ ቢያድር ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የለውም።
[7] ሽመመን እና አፋናሲየቭ በመጽሐፎቻቸው የሚታገሉት አንዱ ነገር ይኽንን ምእመናንን ያገለለ ሊቱርጊያ ነው። የዛሬ ሐምሳ ዓመት ያደረጉት ጥረት ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ፍሬ እያፈራ ይገኛል።
[8] በሚያሳዝን ኹኔታ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሌሎች አብያተ ክርስቲያን ከሚታወቁባቸው ነገሮች አንዱ ለቅዱስ ቍርባን ያላቸው የተሳሳተና superstition የተቀላቀለበት አመለካከት ነው። አቡነ ሺኖዳ ሣልሣዊ ኢትዮጵያ መጥተው በቀደሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሞልቶ ካስቀደሰው ሰው መካከል የሚቆርቡት እፍኝ የማይሞሉት መኾናቸውን ሲያዩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ጳውሎስን “እናንተም እየቀለዳችኹበት ነው፤ ሕዝቡም እናንተ ላይ እየቀለደባችኹ ነው” ብለው ባዘነ ልብ እንደወቀሱ ይነገራል።
[9] Paul F. Bradshaw, et al., The Apostolic Tradition: A Commentary (Fortress Publishers, 2002); L.W. Barnard, The First and Second Apologies, Ancient Christian Writers : The Works of the Fathers in Translation (Paulist Press, 1997).
[10] Susan Ashbrook Harvey, “Training the Women’sChoir: Ascetic Practice and Liturgical Education in Late Antique Syriac Christianity,” in Education and Religion in Late Antique Christianity, ed. Jacob Lollar (Brill, 2020), 204.
[11] ያዕቆብ ዘሥሩግ ምእመናን በንቃት እንዲያዳምጡና እንዲሳተፉ ያሳስብ ነበረ። Harvey, “Training the Women’sChoir: Ascetic Practice and Liturgical Education in Late Antique Syriac Christianity,” 205.
[12] ለምሳሌ፣ ኢሎን መስክ ትዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር የገዛበት መንገድ በሕግ ቅቡልነት ያለው ቢኾንም መንፈሱ ግን ትዊተርን በቁጥጥር ሥር የማዋል ጦርነት አድርገው የሚቆጥሩት አሉ።
[13] Alexander Schmemann, For the Life of the World (Crestwood, New York, 1963), 15.
[14] የቅዱስ ቍርባን ቅዳሴን ምንነት ለማጤን Mebratu Kiros Gebru, አኰቴተ ቍርባን (Akwotetä Q̣urban) (Jajaw Publishers, 2013).
[15] ለምሳሌ፣ ከአስራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን የተገኘ አንድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፈ ሰዓታት በቀን ውስጥ ለ14 የጸሎት ሰዓታት የተመደበ ጸሎት አለው። Ethiopic Manuscripts No. 5, Library of Congress ተመልከት።
[16] ፍትሐ ነገሥት፣ አንቀጽ 14፣ 542 ተመልከት።
[17] Ethiopic Manuscripts No. 5, Library of Congress
[18] Robert Taft, The Liturgy of the Hours in East and West: The Origins of the Divine Office and Its Meaning Today (The Liturgical Press, 1993).
[19] Emmanuel Fritsch, “New Reflections on the Image of Late Antique and Medieval Ethiopian Liturgy,” in Liturgy’s Imagined Past/s: Methodologies and Materials in the Writing of Liturgical History Today, ed. Teresa Berger and Bryan D. Spinks, A Pueblo Book (Liturgical Press, 2016); Emmanuel Fritsch and Habtemichael Kidane, “The Medieval Ethiopian Orthodox Church and Its Liturgy,” in A Companion to Medieval Ethiopia and Eritrea, ed. Samantha Kelly (Brill, 2020).
[20] ፍትሐ ነገሥት፣ በእንተ ጸሎት፣ አንቀጽ 14፣ 545-550.






ይህንንም ለንባብ እንዲመች በpdf አድርጋችሁ ብታጋሩን
አጭሬ ግጥም ቁመተ ዶሮ
የሚንጠራራ ወደ ሰውሮ……..
በአጭሮ እምቅ ሀሳቦች ከነመፍትሄዎችእና ይሁንታዎች የተነሱበት ጽሁፍ ነው፡፡ ትንሽ ቢጎላ ብዬ የማነሳው ለዚህ ሁሉ መፍትሄው የቤታችን መዋቅራዊ አሰራርና መዋቅሩ ላይ ያሉ ሰዎች የሚመጥኑ ባለመሆናቸው በየጊዜው ለሚነሱ ችግሮች ቶሎ መፍትሄ ከመስጠት በሌላ ፖለቲካ ስለተጠመዱና ቤ/ንንም ማዳከም ላይ በመሆናቸው ምእመኑም ሆነ “ሰባኪያኑ” እሳት ማጠፋት ላይ ማለትም እንደ አረም ለቃሚ የፊት የፊቱ ላይ ብቻ ስለምናተኩር ነው፡፡ አሁንም አእላፋት ዝማሬን ወደ አእላፍ ሰአታት ወይም ወደ አእላፍ ቅዳሴ በያሉበት ደብር ብንቀይረው መፍትሄውን የቤ/ን መዋቅር ይዞት ከፊት መምራት ካልቻለና በጎበዝ አለቃ የምንመራ ከሆነ መፍትሄ ብለን የምንወስደውም ሌላ ችግር እየወለደ ነው የሚሄደው ፡፡ ስለዚህ ወቅቱን የዋጀ መዋቅራዊ ለውጥ ለቤ/ን ያስፈልጋል ቤተክርስቲያናችን ብዙ ጣጣ ውስጥ እየገባች ያለችው በመሪ እና በአመራር እጦት ነው ህዝብ መሪውን ነው የሚመስለው ፡፡ መሪዎቻችን ሌላ አለም ላይነው ያሉት እኛም ሌላ አለም ላይነን ፡፡ በጣም የወደድኩት ነገር “ስርአተ አመልኮን ” ማዕከል ያደረገ እይታ ማድረጋችሁ ያለውቅነውን ብዙ እንድናውቅ አድርጎናል፡፡ በነገራችን ላይ በቅዳሴ ዙርያ የሰራችሁትን ፖድካስት እያየሁት ነው ጥሩ ነው፡፡ እናንተ ደግሞ “ኦርቶዶክሳውያንን ወደ ቅዳሴና ሰአታት/ማህሌት የመመለስ ንድፈ ሀሳብ” ብላችሁ ባላችሁበት ሰንበት ት/ቤት የአጥቢያ ምእመናን ወደ ቅዳሴ የማብዛት የማምጣት ስራ ለመስራት ብትነሱና ልክ እንደ ኢጃት እናንተም በሌላ መስመር የራሳችሁን ጡብ ለማስቀመጥ ብትሞክሩ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም “ህዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍታል” እንደተባለው ብዙ ካስተማርን የሚድኑ ነፍሳት ይኖራሉ፡፡ይህንንም ሀሳብ መለዋወጥ የቻልነው የሆነ ስራ ለመስራት የሚመሞክሩ ሰዎች ስላሉ ነው (ያው የመዋቅሩ ችግር እንዳለ ሆኖ) ፡፡ ቅድሚያ ግን..እንደ ዝንጆሮዋ መጀመርያ የመቀመጫችንን (የመሰንበታችንን ) ነገር ላይ ትኩረት ብንሰጥ ጥሩ ነው ጊዜው የለቅሶ ነው መሆን ያለበት፡፡
እውነታው ፍንትው ተደርጎ ተቀምጦልናል። የኔ ሃሳብ፡ ምዕመኑን እንዲህ እንደ አዕላፋት ዝማሬ በቀላሉ ለሰዓታትና ለቅዱስ ቁርባን(ለቅዳሴ) የሚተጋበት መንገድ በማመቻቸት የበኩላችን ጥረት በየአጥቢያችን ለምን አንጀምረውም። ትክክለኛ የክርስቶስ ፍቅር ያገበራቸው መምህራንስ ለምን በየአድባራቱ እንዲሰራጩ መንገዶችን መጥረግ ለምን አንጀምርም።
ይህን ስፅፍ እኔ ካለሁበት ጭው ካለ ገጠር ቤተክርስቲያን እንኳ ከማስተውላቸው የልማድ አካሄዶች ከከተማም ጭምር በሚጋበዙ መምህራን አካትቼ በመነሳት ነው። ይህ ዓይነቱ ያልተገባ አካሄድ ለማስተካከል ብቻዬ ሆኜ ተስፋ ቆርጬ የፈጣሪን የማስተዋል ጥበብን መማፀንን ነው የያዝክሁት። እናንተስ???
በጋዜጣ ቢወጣ ለብዙ ሰው ይደርሳል
በጣም ጥልቅ ትንታኔ ነው፡፡ ብዙው ሃሳብ አሳማኝ ቢሆንም ግእዝ ቋንቋን እና ዜማውን ባእድ እና የማይደረስበት አድርጎ ከመሳል ትውልዱ ቋንቋውን በቀላሉ የሚያውቅበትን ዘመናዊ አሰራር ጠቁሞ በአባቶቹ መንገድ እንዲሄድ ማመቻችት ይሻላል እላለሁ፡፡
ተመሳሳይ ዋና ችግር እኮ የህዝቡ ከቅዳሴው መገለል ላይ አለ ከሰአታቱ ጋ ብቻ ተገናኝቶ ለሱ ብቻ የመፍትሄ ሀሳብ መጠቆም ብቻ ጥሩ መፍትሄ አያረገውም ቅዳሴውን ማዕከል በማድረግ ቅዳሴውን ህዝቡ እንዲያቀው እንዲረዳው እንዲሳተፍበት ቅድሚያ እኮ መሠራት ያለበት መፍትሄም ለችግሮቹ መሰጠት ያለበት ይመስለኛል የቋንቋው ችግር (በሆነ መንገድ ቅዳሴውን በደንብ እንዲረዳው አለመደረጉ) የሰአቱም( በለሊት መገባቱ) ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረት መደረጉ( የቅዳሴው አካል ያልሆኑ አውደምህረት ተኮር ጉዳዮች) የቅዳሴን ነገረ መለኮት ህዝቡ አለመረዳቱ እኚን ነገሮች መፍትሄ ባልሰጠ ሁኔታ ለሰአታቱ ጉዳይ ላይ ብቻ መፍትሄ መጠቆም በዋናነት ለውጥ ሚያመጣ አይመስልም ይልቁኑ የቅዳሴው ተግዳሮት በመሠረታዊነት ከተቃለለ ህዝቡ እስከዚያው ቢያንስ ከቅዳሴው ካልተለየ የሰአታቱን የመፍትሄ ሀሳቦች የቅዳሴው አካል ማድረጉ ቀላል እየሆነ ይሄዳል ቢያንስ ሰው ከዋናው አምልኮ ከቅዳሴ ጨርሶ ባለ መጥፋቱ ከመዳን አይጎልም
መፍትሄው ቅዳሴውን ከህዝቡ የለየውን ችግር ያልነጠለ ያማከለ የቅዳሴውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ማዕከል ባረገ መልኩ የሰአታቱን ጋ የተነሱት የመፍትሄ ሃስቦች ያካተተ ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር እንደእኔ
ጥሩ እይታ ነው የበዛው የአምልኮ ስርዓታቸው ‘መዝሙር’ የሆኑት protestants እኛንም እንደራሳቸው መዝሙር የአምልኮ ስርዓታችን ዋናው መስሏቸው ለቅዱሳን የምናደርገውን ዝማሬ ተመርኩዘው ፍጡር ታመልካላችሁ ይሉናል ይሄን የፈጠረው እንዳነሳኸው ወደ ዝማሬው ያደላን ሆነን ነው ማለት ነው?
ጥሩ ነው ጸሎቲ ወደ አማርኞ ተተርጉሞ በአማርኛ ቢዜም ብዙ ለውጥ ያመጣል እንደ አካባቢውም በየቋንቋው worship should be in the venicular እንደሚሉት አበው አንዳንዶች የግዕዙን ዜማ ያሳጣናል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ ይሄም እውነትነት አለው ታዲ ነገሩን እንዴት እናስኬደው የሚለው የቢተ ክርስቲያን ልጆች ሊወያዩበት ይገባል እኒም ልጅ እያለሁ ፍልሰታን ሳስቀድስ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች መጽሐፍትን በአማርኛ እጸልይ ነበር የዛሬ 37 አመት ከሀገር ስወጣ የምወደው አያቴ በእጅ የምትያዝ ቤተ ክህነት ይሳተማትን የቅዳሴ መጽሐፍ በእማርኛን በግዕዝ በስጦታ መልክ ሰጠኝ የአማርኛውን ትርጉም ባየሁት ጊዜ እጅግ ደነቀኝ ለካ ይሄንን ነው እንዴ የሚጸልዪት በማለት እጅግም ፍቅር አደረብኝ ግዕዝም በወቅቱ እየተማርኩኝ ነው ግን ከባድ ነው ሰውን ሁሉ ግዕዝ ተማሩ ካልን ወጣቱን እናጣዋለን
ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ልክ ትሰፋ ወይስ ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ልክ ይሰፉ?
እንዲህ ዐይነት ቃለ ተዋስኦ ለመፍትሔ እንዲመጣ የሚያግዙ ይመስለኛል፡፡ በሁለቱ ጽሑፎች የተመለከትሁት ያገላለጥ ነገር ሊኖር ቢችልም የጋራ ድምዳሜያቸው ግን ብዙም አይራራቅም፡፡ ይኸውም ‹‹ምዕመናን ከሥርዐተ አምልኮው ወይም ከሉቱርጊያ እንዳይርቁ በልካቸው ወይም በሚገባቸው ነገር ይሠራላቸው(ይቅረብላቸው)›› የሚል ድምዳሜ የያዘ ነው፤ በተለይ ይህ መጣጥፍ የሚደመድመው፡፡
ነገር ግን ከአቋቋም ዜማ ከባድነት እና ከቋንቋው ባዕድነት ብሎ ካነሳው ነገር ባሻገር እንደመፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው ‹‹ማድረግ የሚገባን ሰዓታት ጸሎትን ከነጥንታዊ የመዝሙረ ዳዊት እና የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባባቱ እንዲሁም ከቀላል አሳታፊ ዜማዎቹ ጋር ወደ ቦታው መመለስ ነው›› የሚለው ድምዳሜ እና የመፍትሔ አቅጣጫ አደገኛ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ችግር አምቷል ካልነው ችግር በላይ፣ ሌላ ችግር የሚተክል ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ስርስቲያን ሥርዐተ አምልኮዋን እያስሄደች ያለችው በቅዱስ ያሬድ ዜማ መሠረትነት በመሆኑ ከነባሩ ትውፊት ያስወጣታል፤ ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያንን በምዕመናን ልክ እንድትሰፋ ያደርጋታል፡፡
ስለዚህ፣ ይህ መጣጥፍም ‹‹አልሸሹም ፈቀቅ አሉ›› ዐይነት ነው፤ አዲስ ዜማ እንፍጠርላቸው ከሆነ የአእላፋት ዝማሬም እያደረጉት ያለው ይህንኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ያሬድ መልክ ከሰጣት ውጭ፣ ሌላ መልክ እንስጥ የሚል አንድምታ አለው፡፡ ሲቀጥል ቅዱስ ያሬድ የደረሰው ሥርዐተ አምልኮ ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ነው ያሰኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ያሬድ ዜማ ውጭ ማየት መልክ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ማድረግ ይመስለኛል፡፡ ችግር እንነቅሳለን ብለን፣ ሌላ ችግር እንዳንተክል እንጠንቀቅ፡፡
በተረፈ ማኅሌት እና ሰዓታትን አንድ ለማድረግ ባይጣር ሁለቱ የተለያዩ መልኮች ነገር ግን የሥርዐተ አምልኮው አንድ አካል ናቸው እንጅ አንድ ዐይነት ይዘትና መልክ አድርጎ ማቅረብ ጭፍን ድምዳሜ ይመስለኛል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በሰፊው መሄድ ይቻላል፡፡የአእላፋት ዝማሬን ክስተት እንነቅላለን ተብሎ፣ ሌላ የአእላፋት ዝማሬ እንዳትተክሉብን፡፡ በዚህ ራሱ ወገባችን ጎብጧል፡፡
እንዴት ናችሁ ወንድሞች፣
ስለአኣእላፋት ዝማሬ ውይይታችሁን ሰምቻለሁ። እኔ በጣም በጣም ነው ያዘንኩት። ሶስት ሰዐት ያለፈ ረጅም ውይይት ወደ ለትንሽ ሰዓታት የምዕመናን ዝማሬ እና ምስጋና ኩናኔያችሁን አቀረባችሁ። ብዙ በልደተ በዓሉ ክርስቶስን የረሳነውን እኛን ለተወሰኑ ሰዓታት ላለፉት ሁለት አመታት ወግ ደርሶን ማህሌት እና ቅዳሴ የማንቆመውን እኛ ለትንሽ ሰዓታት እግዜርን በዝማሬ አመሰግንን። እንደ እግዜር ፈቃድ እና እርዳታ ደግሞ ማህሌት፣ ቅዳሴ እና ምስጢር እንቆማለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ማንም በሁለት እግር ተፈጥሮ የቆመ፣ የዘለለ እና የሮጠ ሰው የለም። የክርስትና ጉዞም እንዲሁ ነው። ይቆርብ የነበረና ማሕሌት ይቆም የነበረ ሰው አእላፋት ዝማሬ ያዘናጋዋል ማለት ደግሞ በጣም የማያሳምንና ውሀ የማይዝ ሃሳብ ነው። ሌላ ያላችሁት በጣም ቅር ያለኝ ከቅዳሴ ላይ ተረፍዶ ተገባ፣ ሰውንም አስቀረ የተባለው ጥናት ላይ ያልተመሰረት አስተያየት ነው። ጥናትና መረጃ ላይ ያለተመሰረተ ሃሳብ አመኔታውን ያሳጣል ለእናነተም ድካም ነው የሚሆነው። እንደክርስትያናዊ ወንድምነታችሁ ደግሞ ስጋታችሁን በጥናት ለሚመለከተው አካል ማሳየት ነው እንጂ በአደባባይ ብዙ ፈተና ያለበትን ክርስትያንንና ቤተክርስትያንን ማወዛገብ ነው። አንድ ለጋ ክርስትያን እናንተን ሰምቶ ቅዳሴ ይደክመኛል አይገባኝም ብሎ ባለፈው የጀመረውን የዝማሬ ምስጋና ቢያቆምስ? ወደቤተክርስትያን ይህ ዝግጅት የራቅነውን እኛን ከወትሮው ወደ ቤተክርስትያንን እንድናውቃት አቅረበን እንጂ አላራቀንም። አሁንም ቢሆን እንደኔ እንደኔ እንደምረዳው አምልኮን ቀነሰ ካላችሁ እንደወጣት እንዲጠነክር የሚጠበቅባችሁንን በተግባር ማሳየት ነው ያለባችሁ። እርስ በእርስ በአደባባይ ያለመረጃ መወቃቀስ ጸጉር ስንጠቃ ነው። እውነት ማበረታታት ነበር የነበረባችሁ። እኔ ብቻ ብዙ ማለት እፈልጋለሁ ግን እሄም ከጠቀመ ብዬ ነው።
ክርስቶስ አሁንም ምህረቱን ያብዛልን።