ኤማሁስ ፕሬስ በተባለ አንድ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ላይ “ከጥያቄዎቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች” በሚል ርእስ የተጻፈ ጽሑፍ አንድ ወዳጄ አጋርቶኝ አነበብኩ። ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከልባቸው የሚጨነቁና የሚቀኑ ወንድሞች በመጻፋቸው ደስ ብሎኛል። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ በጽሑፉ ሐሳብና መንፈስ ላይ ግን አስተያየቴን እንድሰጥ ግድ ብሎኛል።
ዘነበ ወላ የተባለው ግለሰብ በተናገረው ነውረኛ ሐሳብ ላይ በጊዜው የጻፍኳትን ትንሽ ጽሑፍ “ተገቢ ያልሆነ” ብለዋታል። ከዚህም በላይ “ከጥያቄዎቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች” ብለው ፈርጀዋታል። ወንድማዊ ብያኔ ስለሆነ ችግር የለውም። ግን ይህች አስተያየት የጻፍኩት እንደዚያ ከማሰኘት የሚያደርሰው ነገር ስላልታየኝ ነው።
እንደ ገባኝ ከሆነ፣ ዋናው ትችት፣ ጽሑፉ ገዳማዊ ሕይወት በኢኮኖሚ፣ በታሪክና መሰል ዘርፎች ያደረጋቸው አስተዋጽኦዎች መጠቀሳቸውና በዚህ አንጻር መልስ መሰጠቱ፣ ገዳማዊ ሕይወትንና ክርስትናን ወደ ምድራዊ እሳቤና መለኪያ ዝቅ የሚያደርግ (reductionist) ነው የሚል ነው። ግን እንደዚህ ብሎ ለመደምደም ይቻላልን?
ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዱቃውያን ቀርበው ስለ ትንሣኤ ሙታን ጉዳይ ጥያቄ በጠየቁት ጊዜ የመለሰላቸው “ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን፣ እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም” ብሎ ነበር። ማቴ. 22፡31-32 ይህ ጌታችን የጠቀሰው ቃል የሚገኘው በኦሪት ዘጸአት 3፡6 ነው። ጌታችን ስለ ትንሣኤ ሙታን ጉዳይ ላነሡት ጥያቄ ሲመልስላቸው፣ ስለ ትንሣኤ ሙታን በግልጽ ከተናገሩት ከነቢያት መጻሕፍት በመጥቀስ ፋንታ ለምን ከዘጸአት ጠቀሰላቸው? ብንል ምክንያቱ ሰዱቃውያን ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በቀር የነቢያትን መጻሕፍት ስለማይቀበሉ ነበር። ስለዚህ ከሚቀበሉት መጽሐፍ ጠቅሶ ስህተታቸውን አስረዳቸው አንጂ ከማይቀበሉት መጻሕፍት ጠቅሶ ላስረዳችሁ አላለም።
ሆኖም ለሰዱቃውያን ከነቢያት መጻሕፍት አለመጥቀሱ ግን የእነርሱን ስህተት በማጽደቅ ወይም ወደ እነርሱ እሳቤ ዝቅ በማለት (reductionism) ያስወቅሰዋልን? ኧረ በጭራሽ! መድኃኒት የሚሰጠው እንደ ሕመሙ ሁኔታና በሽተኛው በሚያስፈልገው ልክ እንጂ በሐኪሙ እውቀት ልክ አይደለምና! አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ደግሞ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ” እያለ አስተምሯል። ማቴ. 5፡17
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን ሲጽፍ የጀመረው “የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” ብሎ የጌታችንን የትውልድ ሐረግ በመዘርዘር ነው። ማቴ. 1፡1 ይህን በማድረጉ ግን ወንጌላዊውን ለምን ስለ ብስራት፣ ስለ ቀዳማዊነቱ “ቀዳሚሁ ቃል” ብሎ አልጀመረም? ተብሎ ይወቀሳልን? ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ወንጌሉን የጀመረው “እነሆ፣ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፣ ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኃጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ . . .” በማለት ስለ ጌታችን ልደትም ሆነ ስለ ብስራት ምንም ሳይል በቀጥታ የጀመረው ከጥምቀቱ ነው። ታዲያ ይህ ወንጌላዊውን የጌታን ብስራቱን፣ የዘር ሐረጉንንና ልደተን አይቀበልም ያሰኘዋልን? በጭራሽ! በኋላ በጊዜው ጊዜ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊውን “ቀዳሚሁ ቃል” ብሎ እንዲጽፍ አደረገው። ሦስቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ) በአብዛኛው ሰው የመሆኑን ነገር ትኩረት አድርገው መጻፋቸው አምላካዊነቱን መዘንጋታቸው አያሰኝም፣ ዮሐንስ ደግሞ አምላካዊነቱን ጎላ አድርጎ መጻፉ ሰውነቱን መዘንጋት አይባልም! አንድን አቅጣጫ ይዞ ብቻ መንጎድ እንደ ተወረወረ ቀስት አደገኛ ነው!
ቅዱስ ጰውሎስም በአቴና ከተማ ከግሪክ ፈላስፎች ጋር ባደረገው አስደናቂ ተዋስኦ ስለ ክርስትና አስተምህሮ በማስረዳት አልጀመረም። ይልቁንም ወደ ክርስትና ያቀርባቸው ዘንድ፣ ምንም እንኳ በከተማው ጣዖታት ሞልተው ማየቱ መንፈሱን በእጅጉ ረብሾት የነበረ ቢሆንም፣ “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ። የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ፣ ለማይታወቅ አምላክ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ” በማለት ጀመረ። ከዚያም “ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፣ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፣ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን” በማለት ከራሳቸው ፈላስፎችም ጠቀሰላቸው። የሐዋ. 17፡22-31 ይህ ግን ያስመሰግነዋል እንጂ እንዴት በቀጥታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከማስተማር አልጀመረም? ይህማ reductionism ነው አያሰኝም!
ስለሆነም በዘነበ ወላ ላይ የተጻፈችው ትንሽ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ስለ ክርስትና “ሀሁ” ለማስተማር ወይም ስለ ምንኩስና ምንነት ፊደል ለማስቆጠር አይደለም። ሆኖም ምናኔያዊ ሕይወት መሠረቱና ዓላማው ቁሳዊ ሀብት ማከማቸትና በዚህ ዐለም መበልጸግ አለመሆኑ ሳይጠቀስ ግን አልታለፈም። ሆኖም የተነሣውን ጉዳይ ችላ ብሎ ባልተነሣ ጉዳይ ላይ ብዙ መድከም ዒላማውን የሳተ ስለሚሆን (ያልበላውን ማከክ እንደሚባለው)፣ በዚህም ላይ ገዳማት በሚባለው ጉዳይ ላይም ቢሆን የሚያኮራ ተጨባጭ ታሪክ የሌላቸው ስላልሆኑ፣ ይህ መብራራቱ “ከጥያቄዎቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች” ሊያሰኝ ይችላልን? መድሎተ ጽድቅ ቅጽ ሦስት ላይ አንድ ምዕራፍ ተሰጥቶ ለመዳሰስ አልተሞከርምን? በፌስ ቡክ አጭር ጽሑፍ ላይ ያን ሁሉ ማብራራት ይጠበቅብኝ ነበረን?
ከላይ ለማንሣት እንደ ተሞከረው አንድን ጉዳይ በብዙ መንገድ ማብራራት ይቻላል። አባ ሶፍሮኒ የመለሱበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው፤ ግን ብቸኛ መንገድ አይመስለኝም። አንዱ ይህን ሌላው ደግሞ ያንን አጽንኦት ቢሰጠው ይደጋገፋል፣ ሙሉ ይሆናል እንጂ እኔ ያልኩትን ካላሉ ወይም በእገሌ መንገድ ካልሆነ በሚል “ከጥያቆቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች” እስከ ማለት መድረሱ አግባብነቱ አልታይህ ብሎኛል።
በዚህ አስተሳሰብ ከሄድን አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ካልገለጸ በቀር፣ “ሌላ የሚያውቀው ግን ያልተናገረው ነገር የለም፣ ይህ ደግሞ ጎደሎነት ወይም reductionism ነው” ወደሚል ጽንፍ እንዳንሄድ ብናስብበት ጥሩ ነው። ይህ ጽሑፋችሁ ራሱ “ከመልሱ በላይ አደገኛ የሆነው መልስ” እንዳይሆን ብታስቡበት ጥሩ ነው።
ስለሆነም ለዘነበ ወላ በአጭሩ ለመስጠት የሞከርኩት መልስ እናንተ እንደምትሉት ገዳማዊ ሕይወትም ሆነ ክርስትና በኢኮኖሚያዊና መሰል ምድራዊ አስተዋጽኦዎቹ ይመዘን የሚል reductionist አይደለም፣ ወይም የገዳማዊ ሕይወትን መሠረታዊ ምነትና ዓላማ ለቁሳዊ መለኪያዎች አሳልፎ የሚሰጥ reductionist አይደለም። ፈጽሞ! ያልተባለውን የተባለ ለማስመሰል ከመድከም ይልቅ ሳይነቅፉ መጻፍ አይቻልም ይሆን? ምናልባት reductionism እንቃወማለን ስትሉ ሌላ ከባድ reductionist እንዳትሆኑ ብታስቡበት ጥሩ ይመስለኛል።
ቤተ ክርስቲያን ዐለሙ በሰፋላት ቀሚስ ውስጥ የመግባት ግዴታ የሌለባት መሆኑ አንድ መሠረታዊና ታላቅ ነገር ሆኖ፣ ዐለሙን መዋጀት ያለባት መሆኑ ደግሞ መዘንጋት የሌለበት ሌላው ጉዳይ ነው! ይህንስ ሌላው reductionism ነው እንበለውን? ጌታችን የተራቡትን እየመገበ የታመሙትን እየፈወሰ ያስተማረው ለምን ይሆን? ቤተ ክርስቲያን ይህ ዐለም የመሥሪያ ቦታዋ አይደለምን? ክርስትናስ ዐለሙን ለመዋጀት የሚችል አስተሳሰብ (ነጽሮተ ዐለም) እና አሠራር የሌለው ይመስል በሰዎች አኗኗርና እሳቤ ውስጥ ድርሻ የለውምን? ለምን ወደ ጓዳ እንዲደበቅ እናደርገዋለን? ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ሕይወት ከበቂ በላይ የሆነውን ክርስትና ለምን ከሙሉነቱ በጎደለ መንገድ እንዲታይ (ወይም እንደዚያ ለሚያስቡት) ግብዓት እንሰጣቸዋለን? በዚህ ዐለም ጉዳይ የማይመለከተው ነውን? ሌሎች እየመገቧቸውና እያለበሷቸው ያሉ ሰዎችን እኛ እናስተምራችሁ ብንላቸው ከልባቸው ይሰሙናልን? የሰዎች ረሃብና ችግርስ ቤተ ክርስቲያንን አይመለከታትምን? የተራቡና የተጠሙ ሰዎችስ ወንጌልን ለመስማት ምን ያህል ዝግጁ ናቸው ይሆን? ብዙ ነገሮችን ማንሣት ይቻላል። ግን ሐሳባችንን ስንገልጽ [እንደ ወንጌላውያን] በአንዱ አጽንዖት ያልተሰጠውን ጉዳይ ሳይነቅፉና ሳይፈርጁ የጎደለ እንኳ ቢኖር በሚሞላና በሚያንጽ መንገድ ቢሆን መልካም ይሆን ይመስለኛል! ለመነቃቀፍ የምናጠፋውን ጊዜ ሌላው ላይ ብናውለው እንዴት በተጠቀምን ነበር!
አሁንም ከሌላ reductionism ይሰውረን! ከዚህ በላይ አልበል!






ቃለህይወት ያሰማልን መምህራችን።በእውነቱ ከሆነ ገዳማት የቤተክርስቲያን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ይኾኑ ዘንድ ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ነን።ገዳማት በልመና መነኮሳት በችግር የሚዋትቱበት ምክንያት ገዳማትን ከኢኮኖሚው ክበብ በማውጣታችን ነው።የግብፅ ገዳማት አቅማቸው የፈረጠመው በልመና አይደለም በምርትና አገልግሎታቸው በሚያገኙት አጥጋቢ ገቢ ነው።
ያደላቸው monastic economy የተሰኘ ፍልስፍና ቀርጸውም ይንቀሳቀሳሉ።
ጽሑፉን አንብቤዋለው ምን ቸገረኝ መሰላችሁ ሁለታችሁም በደንብ አንባቢ ናችሁ ብዬ አምናለው አውቃለውም ግን ምልከታዬን ለማስቀመጥ እይታ የምንመልስበት መንገድ ቢስተካከል ደስ ይለኛል( የትንሽ ወንድማችሁ ምልከታ ነው)።
ተምረናል
መምህር እግዚአብሔር ያክብርልን።በእውነቱ በዘነበ ወላ በተባለ ግለሰብ የተሰጠው ነቀፋዊ ሀሳብ የሚያተኩረው በስራ ላይ ነውና መነኮሳት ከስራ አንጻር ለዓለም የሰጡትን ወይም ያበረከቱትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መግለጽ በመጣበት መመለስ እንጂ ይህ ብቻ ነው የምንኩስና ጥቅም ማለት አይደለምና።አንዳንዴ ሂስ የምንሰጥበትን ሁኔታ ከግምት እያስገባን እላለሁ።ወንድሞቻችን ላነሳችሁት ጥያቄ እግዚአብሔር ያክብራችሁ።
የእኔ ስሜት ተመስገን ዋና ጠቀሰልኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ!
መምህር ያረጋል ቃለ ሕይወትን ያሰማልን በእውነት ቤተክርስቲያን በብዙ አይነት መንገድ ስታይ ወደ ፖለቲካ ውሰጥ ገብታለች። የተሰጠው ምላሸ ግን ፍቅር በተሞላ መንፈስ ስለሆነ ከሁሉ በላይ አእምሮን የሚቆጣጠር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለሁሉም ለቤተክርስቲያን ልጆቿ/ች ከፖለቲካ ወተው/ን ለተጠራንበት አለማ እንድንኖር ያድርግልን።
በድጋሚ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን በእድሜ በጤና ይጠብቅልን።
መምህር ያረጋል አበጋዝም ሆነ በኤማሁስ ሕትመት የምታገለግሉ ወንድሞች ለቤተ ክርስቲያን ካላችሁ መልካም ቅንነት መሆኑን በጽኑ እገነዘባለሁና እግዚአብሔር በመንፈስቅዱስ ሀብት ይጠብቅልን እላለሁ። ነገር ግን መምህር ያረጋል በዳግም መልሳቸው ከሰጡት “በአንዱ አጽንዖት ያልተሰጠውን ጉዳይ ሳይነቅፉና ሳይፈርጁ የጎደለ እንኳ ቢኖር በሚሞላና በሚያንጽ መንገድ ቢሆን መልካም ይሆን ይመስለኛል! ለመነቃቀፍ የምናጠፋውን ጊዜ ሌላው ላይ ብናውለው እንዴት በተጠቀምን ነበር!
አሁንም ከሌላ reductionism ይሰውረን!” እጋራለሁ።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን የጎደለውን መሙላት ይሻላል የጎደዳደውን እንደሞሉ አርገን እንቀበላቸው።
በልኩ መተራረሙንም እንውደደው ።
Rock church of lalibela built b/n 7th _13 th centuries…and protestant reformation began in 1517. We ethiopian orthodox go earlier than the rest of world on cristanity. Google it. 🙏
“አንዱ ይህን ሌላው ደግሞ ያንን አጽንኦት ቢሰጠው ይደጋገፋል፣ ሙሉ ይሆናል እንጂ እኔ ያልኩትን ካላሉ ወይም በእገሌ መንገድ ካልሆነ በሚል “ከጥያቆቹ በላይ አደገኛ የሆኑት መልሶች” እስከ ማለት መድረሱ አግባብነቱ አልታይህ ብሎኛል። ” መምህር ልቅም ያለ መልስ ሰጥተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ተዋሥኦ እንዲለመድ በመሻት ቢሆንም ቅሉ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከምላስ ላይ ፀጉር ነቀላ የሚመስሉ ሀሳቦች የተነሱ ይመስለኛል፡፡ ብታስቡበት መልካም ነው። በተረፈ በርቱ ብዙ እየተማርኹ ነው።
መምህራችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
የኤማሁስ ፕሬስ ሀሳቡን ማቅረባችሁ መልካም ነው ነገር ግን ጥያቂዎችን በመስጠትና በመመለስ ብዙ እየሰሩ ያሉ መምህራንን ጊዜ እየተሻማን ወደ ኋላ እንዳንጎትት የሚል ስጋት ሰሰላለኝ ነው
“አሁንም ከሌላ reductionism ይሰውረን” እጋረዋለሁ
መልካም ሀሣብ ነው መምህር እናንተም የምታነሱት ሀሣብ ጥሩ ነው ከዚህ በፊትም በሄኖክ ሀይሌ (በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ እና በአቡነ አረጋዊ ጽሁፍ) ሀሣብ ላይ Reductionism ተነስቶ ተመልክተናል በዚህም የ Reductionism ሀሣብ ከመለጠጡም በላይ ቤተክርስቲያንን ከአለም የማዉጣትና የምዕመናንን ማህበራዊ ና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የዘነጋ ይመስላል። ስለዚህም በአንድ Podcast ጽንሠ ሀሣቡን ብትዳስሱት መልካም ነው በተረፈ ብዙ እያስተማራችሁን ስለሆነ በዚሁ ቀጥሉ ሀሣብን በሀሣብ መሞገት ይልመድብን ከናንተ ብዙ እንጠብቃለን
ጊዜው የጦርነት እንጅ የልምምድ አይመስለኝም። ሁሉም ተባብሮ ቤተ ክርስቲያንን በሚወጋበት በዚህ ወቅት የራስህ ወገን አንተን ኢላማ ማድረግ ጤንነት አይመስለኝም። ለምሥጢርና ርቃቄው ከሰነበትን እንደርሳለን። መ/ር ያረጋል ምን ብሎ መመለስ ነበረበት? መፍትሔው አድርጎ ማሳዬት እንጅ ከማንም ቀድሞ በጥብአት መልስ የሰጠን የራስ ወገን መውጋት አይመስለኝም።
It is well