ክፍል ፪፡ ወደ ርስታችን ያልተመለስንበት ኢዮቤልዩ

“ከጥንት ጀምሮ የኖሩት የሁሉም ማኅበራተ ሰብእ ታሪክ የመደብ ትግሎች ታሪክ ነው ።”[1]

ዐብዮታውያን ጓዶች የዚህን ጥቅስ ባለቤቶች አያጧቸውም ። ካርል ማርክስ እና ፍሬድሪክ ኤንግልስ – የኮሚዩኒስት ፓርቲ ማኒፌስቶ ምዕራፍ አንድ ፣ ቁጥር አንድ[2] ። ይህች ጥቅስ ከማርክሳዊነት የመዓዝን ድንጋዮች አንዷ ናት ። ማርክሳውያን ‘ታሪካዊ ቁስ አካልነት’ (Historical materialism) ብለው የሚጠሩት ፅንሰ ሐሳብ በዚህች አባባል ይጠቃለላል ። ታሪካዊ ቁስ አካልነት ለማርክሳውያን የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ የሚገዛው ዋና መርሕ ነው ። ነገር ግን እሱን ለመረዳትእና ለመበየን ሌላ መፍቻ ቁልፍ ያስፈልጋል ። ይኸውም ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊነት (Dialectical materialism) ተብሎ የሚጠራው የማርክስ እና የኤንግልስ ፍልስፍናዊ መነሻ ነው ።

ዳያሌክቲካዊ ቁስ አካላዊነት የሁለት ፅንሰ ሐሳቦች ውጤት ነው ። ምንነታቸውን ራሳቸውን ባለቤቶቹን ጠይቀን እንረዳለን ። ከቁስ አካልነት እንጀምር ። በዐብዮታዊው መንግሥታችን የተዘጋጀው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ስለ ቁስ አካልነት እንዲህ ይለናል ፥

“ቁስ አካልነት የተመሠረተው ዓለም ቁሳዊ ባሕርይ ያለውና ቁስ አካልም ያልተፈጠረና ዘላለማዊ የሆነ ኑባሬ ነው በሚለው አስተምህሮ ላይ ነው ። ማንኛውም ነገር ቁስ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ የሚመነጨውና የሚያድገው ከቁስ አካልና እሱን ከሚገዙ ሕጎች ነው ። ነገሮች ሁሉ የቁስ አካል የተለያዩ መልኮች ናቸው ። ቁስ አካል ነባራዊ እውነታ ፤ ከሐሳብ ፍላጎት ውጭ የሆነ ነፃ ህልውና ያለው ነው ። የቁስ አካል ነባራዊነት የሰውን ልጅ ዕውቀት ነባራዊ ያደርገዋል ። ዓለምና ዓለምን የሚገዙ ሕጎች በሰው ሊታወቁ ይችላሉ ።”[3]

“Marx’s philosophical materialism holds that the world by its very nature material, that the multifold phenomena of the world constitute different forms of matter in motion that interconnection and interdependence of phenomena as established by the dialectical method, are a law of the development of moving matter, and that the world develops in accordance with the laws of movement of matter and stands in no need of a “universal spirit.””[4]

የቁስ አካልነትን ነገር እዚህ ጋ እንያዘውና ወደ ሌላው ክፍል እንሒድ – ዳያሌክቲክስ ። ዳያሌክቲክስ እንደ ቁስ አካል ይህ ነው የሚባል ነገር ሳይሆን ቁስ አካልን መመልከቻ መነጽር ነው ። ቁም ነገሩ ቅራኔ ነው ።

“ቅራኔ የቁስ አካላዊ ዲያሌክቲክስ መሠረታዊ ፈርጅ ነው ፤ ምክንያቱም ቅራኔ የማናቸውም ነገር አንቀሳቃሽ ኃይልና የዕድገትን ምንጭ የሚያሳይ በመሆኑ ነው ።”[5]

ጓድ ስታሊንም እንዲህ ይለናል ።

“(The dialectical method) regards the phenomena of nature as being in constant movement and undergoing constant change, and the development of nature as the result of the development of the contradictions in nature, as the result of opposed forces in nature.”[6]

ይህ ቅራኔአዊ ዘይቤ ፣ እንደማርክሳውያን አባባል metaphysics (ዲበ አካላዊ ተብሎ ተተርጉሟል በቀጥታ) ከምንለው ዘይቤ የተቃረነ ነው ። በአጭሩ metaphysics “ከቁስ አካል ባሻገር ምን አለ ?” ብሎ መጠየቅ ነው ሥራው ። ቁስ አካል ፍጹማዊ እና በራሱ ያለ ነው የሚለውን መነሻ የሚጠይቅ የፍልስፍና ዘርፍ ነው ። ስለዚህ እነ ማርክስ ቅራኔአዊ ዘይቤአቸውን የሚያመጡት ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ እና ምርምር ተቃራኒ አድርገው ነው ። ከቁስ አካል ባሻገር መመልከት ዋጋ ቢስ ነው ፤ ይልቁንም ነገሮችን መመልከት ያለብን በተፈጥሮ – በቁስ አካል – ውስጥ ያለውን ለውጥ እና እንቅስቃሴ – ወይም ደግሞ ቁስ አካል ራሱ ዘወትር የሚኖርበትን ለውጥ እና እንቅስቃሴ ነው ባይ ናቸው ። ይህ ለውጥ ደግሞ በቁስ አካል ውስጥ ካለ የማያቋርጥ ቅራኔ – ወይም ዘወትር በቅራኔ ከሚኖሩ ኃይሎች የሚመነጭ ነው ። ይህ ዓይነቱ የማያቋርጥ ቅራኔ ነው ወደ ዕድገት የሚመራው – በስምምነት ዕድገት የለም ።[7]

ነገሩ በተጠየቅ ወደ ብዙ አቅጣጫ ሊመራ የሚችል እና ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው ። ነገር ግን ዓላማችን በዋናነት የማርክሳዊነትን መሠረታዊ መነሻዎች መረዳት ስለሆነ በጥቂት ነጥቦች እንቆጠብ ። የሚከተሉት ነጥቦች ከሞላ ጎደል ማርክሳውያን ራሳቸው የሚስማሙባቸው ናቸው ።

  1. ያለው ቁስ አካል ብቻ ነው ። ይህ እንደመሆኑ ደግሞ ከቁስ ባሻገር ምንም የለምና – ከቁስ አካል ጀርባ ፈጣሪ የለም ። ከቁስ አካል ባሻገር – ቁስ አካላዊ ያልሆኑ መንፈሳዊ ህላዌዎችም የሉም ።ሐሳቦችም ሆኑ ኅሊና የቁስ አካል መልኮች እንጂ የተለየ ህላዌ የላቸውም ።
  2. ቁስ አካል በሆኑ በማይለወጡ ሕጎች ይገዛል ።
  3. በተፈጥሮ ያሉ ነገሮች ለቅራኔአዊ ሕግ ተገዢ ሆነው ይኖራሉ እንጂ ሊሠምሩ እና በሥምረታቸው ውስጥ ዕድገትን ሊያገኙ የሚችሉ አይደሉም ። ስለዚህ ዕድገት የሚመታው አንዱ ሌላውን በማሸነፉ እና በማጥፋቱ እንጂ በስምምነት እና በሥምረት አይደለም ።

ስለዚህ ማርክሳዊ ለመሆን – በቁስ አካል ብቻ ህላዌ ማመን ፣ የእግዚአብሔርን መኖር መካድ ፣ እና በዘላለማዊ ቅራኔ ማመን የግድ ነው ። እነዚህን ሐሳቦች ስንከተላቸው ደግሞ ነጻ ፈቃድን ወደ መካድ ፣ ስነ ምግባርን ወደ መካድ ያደርሱናል ። ምክንያቱም ያለው ነገር ሁሉ (ሐሳቦች እና ኅሊና ሳይቀሩ) ቁስ አካል ብቻ እንደመሆኑ እና ቁስ አካል ደግሞ በተወሰኑ ሕጎች የሚገዛ እንደመሆኑ ነጻ ፈቃድ የሚባል ነገር የለም – ውሃ ከከፍታ ወደ ዝቅታ እንደሚፈስስ እና ስለመፍሰሱም ሆነ ስለሚፈስስበት መንገድ አማራጭ እንደሌለው ሁሉ ሁነቶችም እንዲሁ አንዱ ከአንዱ እየተከታተለ ይሆናል ። ከሆነው እና ከሚሆነው ሌላ አማራጭ ፣ ሌላ የመሆን ዕድል እና የታሪክ መንገድ የለም ። እንዲሁ ሰውም የሚያስበውን ከማሰብ የሚናገረውን ከመናገር እና የሚያደርገውን ከማድረግ ፣ የማያደርገውንም ካለማድረግ መቆጠብ አይችልም – እሱም ሁለመናው ቁስ አካል ነውና ። በቁስ አካልነቱም ቁስ አካልን ለሚገዙ ሕጎች ይገዛል ። ስለዚህም በጎ ወይም ክፉ ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ሊባል የሚችል ሁነት ወይም ህላዌ የለም ።

እዚህ ጋ እነዚህ የማርክስ መነሻዎች እንዴት ከማርክሳዊ ግቦች እና መንገዶች ጋር በቀጥታ እንደሚቃረኑ የተወሰነ ልል እችል ነበር ፣ ለማለትም እወድ ነበር ። ነገር ግን ከመንገዳችን እንዳያስወጣን እተወዋለሁ ።

እንግዲህ ታሪካዊ ቁስ አካልነት ብለን ከላይ ነገራችንን የጀመርንበት ፅንሰ ሐሳብ እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ቁስ አካልነትን እና ቅራኔአዊ ዘይቤን ወደ ማኅበራዊው ዓውድ በማምጣት የሚገኝ ነው ። ውጤቱም ከላይ ያየነው – የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ሁሉ መደባዊ ትግል ነው የሚል ነው ። መደብ ምንድነው ትሉ ይሆናል – ዐብዮታውያን ያልሆናችሁ ጓዶች ። ወዲህ ነው ነገሩ ።

እንግዲህ ሁሉም ነገር ቁስ አካል ከሆነ እና ዘወትር በቅራኔ የሚኖር ከሆነ ሰውም ከነኅሊናው እና ከነሐሳቦቹ ቁስ አካል ነውና እንዲሁ ዘወትር በቅራኔ በለውጥ እና በእንቅስቃሴ መኖሩ የግድ ነው ። ጓድ ስታሊን እንደሚያብራራው ደግሞ – የማኅበረ ሰብእን ለውጥ እና ዕድገት የሚያመጣው የሰውን ልጅ ህላዌ ለማስቀጠል የሚያስፈልጉ ነገሮችን (ምግብ ፣ ልብስ ፣ መጠለያ ፣ ነዳጅ ሌሎችም የምርት መሣሪያዎች) በሚያስገኙ የምርት ዘዴዎች እና ቁስ አካላዊ ዕሴቶች ዙሪያ የሚደረግ ቅራኔ ነው ።[8] ይህ ቅራኔ ሁለት ደረጃዎች ያሉት ነው ። በመጀመሪያ ሰው እነዚህን ለማግኘት ከተፈጥሮ (ከሰው ውጭ ካለው ቁስ አካላዊ ህላዌ) ጋር ቅራኔ ውስጥ ይገባል ። ሁለተኛው ቅራኔ ደግሞ በሰዎች መካከል እነዚህ ነገሮች ለማካበት የሚደረገው ሽሚያ ነው ።[9]

መደቦች ይህን ሽሚያ የሚያደርጉት ቡድኖች ሲሆኑ የመቧደናቸው መሠረት እና የማንነታቸው መገለጫ በምርት ሒደት ውስጥ ያላቸው ቦታ ነው ። ለምሳሌ በጋርዮሽ ዘመን የሰው ልጅ ሁሉ ትኩረት ተፈጥሮን ማሸነፍ ላይ ስለነበረ ወደ እርስ በእርስ ፍትጊያ አልተገባም ነበር ። ስለዚህም በወቅቱ መደቦች አልነበሩም – የመደብ ትግልም አልነበረም ። ታሪክም አልነጋም ።

በኋላ ግን ተፈጥሮ በተወሰነ መልኩ ድል ተደርጋ ቋሚ የሆኑ የምርት ምንጮች በሰው ልጅ ቁጥጥር ስር ሲውሉ ከመካከል የተወሰኑ ሰዎች የምርት ሒደቱን በፍጹም የበላይነት በመቆጣጠር – ከተፈጥሮ የተገኙትን የምርት ግብዓቶችም ሆነ አምራቾቹን ሰዎች ንብረት በማድረግ የባርነትን ሥርዓት ይፈጥራሉ ። በዚህ ጊዜ ባሮች አንድ መደብ – ጌቶች ደግሞ ሌላ መደብ ይሆኑና የመደብ ትግል ይጀምራል ። ነገር ግን ከተፈጥሮ ጋር ያለው የምርት ትግል ፣ እንዲሁም በመደቦች መካከል የሚደረገው ፍትጊያ ሁሌም ቢሆን “ወደ ተሻሉ” የምርት መንገዶች ይመራል – ስለዚህ ቀድሞ የነበረው የምርት ሥርዓት ከውስጡ በወጣ ሌላ ሥርዓት ይተካና ይጠፋል ። አዲስ መደቦች ይፈጠራሉ ። ነገር ግን ሁሌም ቢሆን የሚፈጠሩት መደቦች ገዢ እኛ ተገዢ ፣ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ መሆናቸው አይቀርም – ዓይነቱ ቢለያይም – ባሪያ እና ጌታ በባለመሬት እና በጭሰኛ ይተካሉ ። እነሱም በተራቸው በቡርዧ ካፒታሊስት (የትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ባለቤቶች) – ከበርቴ ተብለዋል – እና በወዛደር (የኢንዱስትሪ ሠራተኞች) ይተካሉ ። ግን የግድ ሁለት መደብ ብቻ አይኖርም ፤ እንደ ምርት ሥርዓቱ ሌሎችም ብዙ መደቦች ይኖራሉ ። ነገር ግን ሁሌም ቢሆን በሁለቱ ዐበይት መደቦች መካከል ያለው ቅራኔ ይጏላል – በዋነት የምርት መንገዶችን የተቆጣጠረው እና በቁጥር ግን አናሳ የሆነው “ገዢ መደብ” እና በቁጥር እጅግ ብዙ ሆኖ እና በምርት ሒደት ውስጥ ዋናውን ሚና እየተጫወተ ፥ የምርት ባለቤትነትን እና ተጠቃሚነትን ግን የተነፈገው “ሰፊው ጭቁን መደብ” ።[10]

ስለዚህ – ዐብዮታውያን ያልሆናችሁ ጓዶች – መደብ ማለት በምርት ሒደት ውስጥ ተመሳሳይ ቦታ ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው ። ምርት የሰው ልጅ ኑሮ መሠረት እና ማዕከል እንደመሆኑ እና በምርት ሒደት ውስጥ ያለ ቦታ የምርት ባለቤትነትን ስለሚያሳይ አንድ ሰው የዚህ ወይም የዚያ መደብ አባል መሆኑ የማንነቱ መሠረት ነው ። ማርክስ እና ኤንግልስ ይህን ሲያጠይቁ ወደኋላ አይሉም ።

“The bourgeoise, historically, has played the most revolutionary part.… It has pitilessly torn asunder the motley feudal ties that bound man to his “natural superiors”, and has left remaining no other nexus between man and man than naked self intrest, than callous “cash payment”…. In one word, for exploitation veiled by religious and political illusions, it has substituted naked, shameless, direct, brutal exploitation.”

ሌላው ቀርቶ የቤተሰብን ምንነትም ጭምር አያስተርፉትም ።

“The bourgeoisie has torn awe from the family its sentimenral veil, and has reduced the family relation to a mere money relation.” [11]

ስለዚህ በጠቅላላው በማንም መካከል ቢሆን የግንኙነት ዋና ምክንያት እና ርእስ የሚሆነው – ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ በሌላ መጋረጃዎች ቢጋረድም ቅሉ – የምርት ተጠቃሚነት ነው – ስታሊን እንደዘረዘረው መብላት መጠጣት መልበስ ወዘተርፈ – በጠቅላላው ክርስቲያኖች ሲያንስ “ቁመተ ሥጋ” ፣ ሲበዛም “ሥጋዊ ምቾት” እያሉ የሚያጥላሉት ሐሳብ ነው ። የመደቦች የቅራኔ ምንጭ ይኸው ነው ። የትብብር ምንጭም ሊሆን የሚችለው ተጨቋኞች የጋራ ጭቆናቸውን አስወግደው የምርት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አንድ ላይ መቆማቸው ነው ። ከሱ ቀድሞ እና በፊት በሁለት ሰዎችም ሆነ ቡድኖች መካከል ሊቆም የሚችል ምንም ነገር የለም – በቤተሰብ መካከልም ቢሆን ።

እንዲህ እያለ ቅራኔው እየቀጠለ ፥ ዓይነቱ እየተለዋወጠ ይሔዳል ። ታዲያ ይህ ሒደት በተወሰኑ ሕጎች የሚገዛ እንደመሆኑ ሊጠና እና ሊታወቅ የሚችል – ልክ እንደ ፊዚክስ እና እንደ ባዮሎጂ ከግምት ባለፈ ሊታወቅ የሚችል ነው ። በመሆኑም በቂ ዕውቀት ስናዳብር ይህ ቅራኔ ወዴት እንደሚያመራ በእርግጠኝነት ልንናገር እንችላለን ።

“The theoretical conclusions of the Communists are in no way based on ideas or principles that have been invented, or discovered, by this or that would-be reformer.

“They merely express, in general terms, actual relations springing from an existing class struggle, from a historical movement going on under our very eyes. The abolition of existing property relations is not at all a distinctive feature of Communism.”[12]

“Hence, the science of the history of society, despite all the complexity of the phenomena of social life can become as precise as a science as, let us say, biology, and capable of making use of the laws of development of sociery for practical purposes.”[13]

ይህን በማለታቸው ማርክስ እና ኤንግልስ እንዲሁም ስታሊን ግልጽ የሚያደርጉልን አንድ ነገር ቢሆን ነገሮችን የተሻሉ ለማድረግ ጥቆማ እየሰጡን ወይም ምኞታቸውን እየገለጡልን ሳይሆን ሳይሆን ነገሮች እንዴት እንደሆኑ እና እንደሚሆኑ እየገለጡልን መሆኑን ነው ። ሆድ ዕቃህን ከፍቶ ከመረመረው ሐኪም ጋር ስለ ጉበትህ ወይም ስለ ጨጓራህ የምትከራከረውን ያህል ነው በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላለው የመደብ ትግል ሁኔታ ከኮሚዩኒስቶች ጋር ልትከራከር የምትችለው ። የአስተያየት ጉዳይ አይደለም – የማይጋፉት እና የማይክዱት እውነታ ነው ።

ሌሎች ብዙ ላነሣቸው የምችላቸው እና የምፈልጋቸው የማርክሳዊነት ገጾች ነበሩ ። ልገጥማቸው የምወዳቸውም ብዙ ሙግቶች ። ግን አሁንም ራሴን ልግታ እና ወደ ነጥቤ ልመለስ ። የማርክሳዊነት መነሻዎች እንዲህ ያሉ ናቸው ። ስለ ኢትዮጵያ “ዐብዮት” ስንነጋገር የምናነሣቸው ጥያቄዎች በእነዚህ ሐሳቦች መሠረትነት የተቀመሩ ናቸው ።

የማርክስን የመደብ ብያኔ ሳይዙ እና ሳይቀበሉ ስለ መደብ ትግል እና ስለ መደብ ጭቆና ማውራት አይቻልም ። ስለ መደብ ትግል በተወራ ቅጽበት – ቁስ አካልነትን ፣ ቅራኔአዊ ዘይቤን ፣ ኢአማኒነትን ፣ የነጻ ፈቃድን አለመኖር ወዘተርፈ እያጸደቅን ነው ። ለምሳሌ ቁስ አካልነትን በካድን ቅጽበት – የምርት ማዕከላዊነት ፣ ስለዚህም የመደብ ትግል ዐቢይነት ብቻ ሳይሆን የመደቦች መኖር አለመኖር ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ ይገባል ። ቅራኔአዊነትን በጣልን ቅጽበት – መደቦች ቢኖሩ እንኳን የመታገላቸው አስፈላጊነት ይቀራል – ምክንያቱም ቅራኔአቸው በስምምነት ሊፈታ ይችላል ።

የብሔር ጥያቄም ሆነ የሴቶች ጥያቄ እንዲሁ ቅራኔአዊነትን ግዴታ ያደርጋል – ቁስ አካላዊነትንም እንዲሁ ። የሰው ልጅ ሕይወት ማዕከል የምርት ባለቤትነት በሆነበትና በምርት ዙሪያ ያሉ ጥያቄዎች በቅራኔ ብቻ በሚፈቱበት ዓለም ነው “ብሔሮች” ከሌሎች “ብሔሮች” ጋር ፣ ሴቶችም ከወንዶች ጋር ጭቆናን የመታገል ግንኙነት የሚኖራቸው[14]

ይህን ስል ፥ ግልጽ ለማድረግ ያህል ፥ ርእዮቶች እና የፍልስፍና ዘርፎች አይወራረሱም እያልሁ አይደለም ። በማርክሳዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ካልሆነ በሌሎች ርእዮቶች ማዕቀፍ ውስጥ ማርክሳዊነት ውስጥ ያሉ ፅንሰ ሐሳቦች ምንም ዋጋ የላቸውም እያልሁ አይደለም ። ቢያንስ ርእዮቶቹ በአንድም በሌላም መንገድ በተመሳሰሉ ቁጥር – ወይም በሚመሳሰሉባቸው ነገሮች የሚዋዋሷቸው ቃላት እና ሐሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ ። ነገር ግን ብዙ ጊዜ በተለይ ዋና ዋና ቁም ነገሮቻቸው የተቃረኑ ስለሚሆኑ ይህ መዋዋስ በከባድ ጥንቃቄ ካልተካሔደ ጥቅም አይኖረውም ፣ ከባድ ጉዳት ያስከትላል እንጂ ።

ለምሳሌ ፥ ምንም ሜካኒካል እውቀት ባይኖረኝም ፥ የመኪናን ሞተር እንዳለ ወስዶ ሌላ ማሽን ላይ – እንበልና ጀነሬተር ላይ መግጠም እንደማይቻል በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ። እንኳን የጀነሬተር ላይ ፣ ሌላ መኪና ላይም ሊገጥሙት አይቻልም ። ምናልባት ይቻላል እንኳን ቢባል በዙ ጭማሪ እና ቅናሽ ፣ ብዙ ለውጥ ከማስፈለጉ የተነሣ – ሥራው ከተከናወነ በኋላ ሞተሩ የድሮው ሞተር ነው ለማለት አይቻልም ። ነገር ግን ነገርየው አካል ለሆነበት ነገር ያለው ልዩ ተስማሚነት (specification) በቀነሰ መጠን ወደ ሌላ አካል ወስዶ ለመግጠም እና ከትንሽ ለውጥ ጋር ወይም ያለ ምንም ለውጥ እንዲሠራ ለማድረግ የሚጠይቀው ሥራ በጣም እያነሰ ይመጣል ። ከመኪና ላይ የተፈታ ብሎን ሌላ ቦታ ወስዶ መግጠም አስቸጋሪ ነገር አይሆንም ።

እርግጥ ነው – መኪና ፣ ጀነሬተር ወይም ሌሎች አንዳች ጥቅም ለማስገኘት የተሠሩ መሣሪያዎችን ፥ በዋናነት የዓለምን ሥሪት ከሚያብራሩት (እናብራራለን ከሚሉት) ከማርክሳዊነትም ሆኑ ከሌሎች ርእዮቶች ጋር የሚያነጻጽር በመሆኑ ምሳሌው ሕጹጽ ነው ። ያም ሆኖ ግን ለማብራራት የተፈለገው ጉዳይ ግልጽ ይመስለኛል ።

ማርክሳዊነት በውስጡ ላሉት – ወይም በዓለም ላይ ለሚመለከታቸው ነገሮች የሚሰጠው ዋጋ ሌላ ርእዮት ከሚሰጠው ዋጋ በእጅጉ የተለየ ነው ። “ምርት” ማርክሳዊነት ውስጥ ያለው ቦታ በእጅጉ ማዕከላዊ ከመሆንም አልፎ የነገሮች ፍጻሜ እንደመሆኑ ፣ ‘የመደብ ትግል’ ፅንሰ ሐሳብ ደግሞ በዚህ የምርት ማእከላዊነት ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ ፣ ሌላ ነገርን ማእከል ወደ አደረጉ ርእዮቶች ወስደን ስናስገባው – ወይ የመደብን ፅንሰ ሐሳብ ለሌላው ርእዮት እንዲገጥም ለማድረግ በማደርግበት ለውጦች ማርክሳዊነት ውስጥ የነበረውን ይዘት እና ዋጋ ያጣል ፤ ስለዚህም በማርክሳዊነት ማዕቀፍ ውስጥ እና በሌላኛው ርእዮት ማእቀፍ ውስጥ ‘መደብ’ ወይም ‘መደባዊ ትግል’ ስንል ተመሳሳይ ነገር ሊሆን አይችልም ። ስለዚህም ከሁለቱ ርእዮቶች አንጻር እያወሩ ያሉ ሰዎች ይህን ቃል ተጠቅመው ከመጯጯህ ባለፈ የማይግባቡበት ሁኔታ ይፈጠራል ። አሊያም ርእዮቱን ‘መደባዊ ትግል’ የሚለውን ሐሳብ እንዳለ ተቀብሎ እንዲያስተናግድልን በምናደርግበት ለውጦች ሌላ ርእዮትነቱ ቀርቶ በዋናነት (essentially) ወደ ማርክሳዊነት እንለውጠዋለን ።

አንድ ሰው እንዲህ ቃልን እና ሐሳብን ከአንድ ርእዮት ስለመዋስ ቀለል አድርጎ ካወራ (በተለይ ደግሞ እንደኛ ዘመን ለሚያስባቸው ነገሮች እና ለያዛቸው አቋሞች ፍልስፍናዊ መሠረት ለመስጠት የማይጨነቅ ሆኖ ሳለ) በቁም ነገር ሊወሰድ የሚገባው ሰው ባይሆን ነው ። ለዚህም ነው ባለፈው ክፍል መጨረሻ ያነሣሁትን እና በዚህ ክፍል መልስ ልሰጠው የሞከርሁትን – ምንም እንኳን ማርክሳውያን ባንሆንም ከማርክሳዊነት ቃልና ሐሳብ መዋሳችን ችግር የለውም የሚለውን ተቃውሞ የማልቀበለው ፤ የነገሩን ክብደት ካለመረዳት የመጣ ባዶ ጩኸት ስለሆነ ።

በኛ ተዋሥኦ ውስጥ ችግር ነው ብዬ የማስበው አንዱ ጉዳይ ከላይ እንዳልሁት በግልጽ ማርክሳዊነትን የሚከተሉም ሆነ በተናጥል ከሞላ ጎደል የማርክሳዊነትን መነሻ ነጥቦች ከሞላ ጎደል የሚቀበሉ ሰዎች አለማየቴ ነው ። ነገር ግን ከማርክሳዊ አመለካከት ያገኘናቸውን ሐሳቦች እና አገላለጾች ያለ ጥያቄ እና ያለ ገደብ እንጠቀምባቸዋለን ። ይህም የተዋሥኦዎቻችንን መክሸፍ ይህ የሚያስረዳ ይመስለኛል ።

በይፋ ማርክሳዊነትን የሚቀበል ጎራ ቢኖር (የተወሰኑ ግለሰቦች መኖራቸው አይጠረጠርም መቼም) ከዚህ ጎራ ጋር ስለ ሁነቶች ከማውራታችን በፊት ስለ መሠረታዊ ነገሮች ቀድመን መስማማት ይኖርብናል ። እነሱ ቁስ አካላውያን ሆነው – እኛ ደግሞ ቁስ አካልነትን እየተቃወምን – ስለ ታሪካዊ ሁነቶች ወይም ስለ ተምኔቶቻችን ልንስማማ አንችልም ። እነሱ ኢአማንያን ሆነው ፥ እኛ ክርስቲያን ሆነን ስለ በጎነት እና ስለ ክፋት ተመሳሳይ እይታ ሊኖረን አይችልም ፤ “ሰው ሊኖር የሚገባው እንዴት ነው ?” ስለሚለው ተመሳሳይ ሐሳቦች ሊኖሩን አይችሉም ። መጀመሪያ ስለ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ስምምነት ሊኖረን ይገባል ። ስለ እነዚህ ነገሮች ስምምነት ሊኖረን ባይችል ደግሞ ሁል ጊዜም ስለ “ወቅታዊ” እና “ተግባራዊ” ጉዳዮች ስንነጋገር እነዚህን መሠረታዊ ልዩነቶች በማጠየቅ ሊሆን ይገባል ፤ የእነሱን ጥያቄዎች እና ሐሳቦች መመለስንም በጥያቄዎቻቸው እና በሐሳቦቻቸው ውስጥ የተቀበሩትን መሠረታውያን ሳንቃወም እና ሳናፈርስ ልናደርገው አይቻለንም ።

እንዲህ መሠረታዊ የሆኑትን ጥያቄዎች ሳያስቡባቸው ወቅታዊ ጥያቄዎችን እና ጥቅመኛ መልሶችን (utilitarian answers) ይዘው የሚመጡ ሰዎችንም መሠረታዊ ወደሆነው ተዋሥኦ መመለስ የግድ ይሆናል ። አለበለዚያ እስካሁን ከቆየንበት የሐሳብ ምክነት ልንወጣ አንችልም ።

[1] “The history of all hitherto existing society is the history of class struggles.”

[2] Engels F. and Marx K. (1975), Manifesto of the Communist Party. Progress publishers, Moscow. P. 40

[3] ኩራዝ (1978) ፣ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት ። ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ፣ አዲስ አበባ ። ገጽ 185

[4] Stalin J. (1975), Dialectical and Historical Materialism. Mass Publication, Culcutta. p. 11-2

[5] ኩራዝ (1978) ፣ ገጽ 425

[6] Stalin J. (1975), p. 4

[7] Ibid, p. 8

[8] Ibid, p. 23

[9] Ibid, p. 24

[10] Ibid, p. 29-32

[11] Engels F. and Marx K. (1975), p. 44-5

[12] Ibid, p. 62

[13] Stalin J. (1975), p. 16

[14] እውነት ነው በ20ኛው ምዕት – በተለይ በ1960ዎቹ – የማርክስ እና የኤንግልስ ሐሳቦች ከመደብ ትግል ውጭ ወደ ብዙ ጉዳዮች – ወደ ቅኝ ግዛት ፣ ጾታ ፣ ዘረኝነት ወዘተርፈ ጥያቄዎች ተወስደው ተስፋፍተዋል ። እንዲያውም እነዚህ መስፋፋቶች ማርክስ እና ኤንግልስ ካሏቸው ነገሮች የሚቃረኑበት ጊዜ አለ ። የሆነ ሆኖ ግን በእኛ ሀገር ለማርክሳዊነት ዋና አብነት የሆኑት ማርክስ ፣ ኤንግልስ ፣ ሌኒን ፣ ስታሊን እና ማኦ ናቸው (Balsvik, p. 265) ። ስለዚህ ለጊዜው ወደዚያ መስመር መንጎድ አያሻንም ።

Share...

Facebook
Telegram
WhatsApp
X
Email
Print
Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Related Posts

Guest Posts
መሐሪ ዘመልአክ

የአእላፋት ዝማሬ ምልክት ነው ።

መግቢያ በዘመናችን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታየው “የአእላፋት ዝማሬ” የተባለው ክሥተት ሰፊ የሆነ ሕዝባዊና ሊቱርጊያዊ ውይይት አስነስቷል። አንዳንዶች ይህን እንቅስቃሴ እንደ መንፈሳዊ ንቃትና የራቁ ምእመናን ተሳትፎ መመለሻ ሲያቀርቡት፣ ሌሎች ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሊቱርጊያ[1] ጋር የሚጋጭ እና ሥርዓታዊ መነሻዋን የሚያዳክም ክዋኔ እንደሆነ ይገምግሙታል። ወንድማችን በርናባስ ሽፈራው የጻፈው “የአእላፋት ዝማሬ”ን የተመለከተ የኤማሁስ ገጽ ጽሑፍ አንዳንዶችን ሲያበሳጭ፣ ሌሎችን ሲያሳስብ እንደሰነበተ በአረቦን ቴሌግራም ቻነል ላይ ተመልክቻለኹ። 23 ገጾችን የያዘ፣ ንዑሳን አርእስት በግልጽ ያልተሰጡት ረዥም ጽሑፍ ስለኾነ ጊዜ ሰጥቶ ማንበብን፣ ካነበቡም በኋላ ዐበይት መከራከሪያዎቹን ማጥለልን ይጠይቃል። እንዲኽም ኾኖ፣ ቢያንስ መሠረታዊ የኾነ የሊቱርጊያዊ ነገረ መለኮት (liturgical theology) ንባብ ለሌለው ሰው ጽሑፉ ከንቱ ምቀኝነት፣ መራራነት፣ አማራሪነት፣ ጠብ ያለሽ በዳቦ ሊመስል ይችላል። በዋናነት እየነቀሰ የሚተቸው “የአእላፋት ዝማሬ”ን ልዩ ልዩ መልኮች ይኹን እንጂ፣ መሠረታዊ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ጊዜ ያለችበትን ሊቱርጊያዊ ቀውስ (liturgical crisis) መጠቆም ኾኖ አግኝቼዋለኹ። ጉዳዩ እኔንም ሲያሳስበኝ የነበረ ነገር ስለነበረ የበርናባስን ሐሳብ እንዲኽ ልለጥቀው ወደድኹ። የእኔ ጽሑፍ የ“የአእላፋት ዝማሬ”ን እንደ ምልክት በመመልከት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ የምትገኝበትን ሊቱርጊያዊ ቀውስ ይጠቁማል። በተለይም በቋንቋ ባዕድነት፣ በዜማ ውስብስብነትና በሰዓት ምቹ አለመኾን ምክንያት ምእመናን ከ“ሰዓታት ጸሎት” የራቁበትን ኹኔታና ኮንሰርታዊ ዝግጅቶች በተግባር የተኩት የሊቱርጊያ ባዶ (liturgical vacuum) ምን እንደሆነ ለማመልከትና መፍትሔውን ለማሳየት ይጥራል። The Problem of Reactive Ministry እና Institutional Survivalism በርናባስ በጽሑፉ የሚተቸው አንዱ ነገር ይኽ ተልእኮን

Read More »
Emmaus Posts
በርናባስ ሽፈራው

“የአእላፋት ዝማሬ”

ሁለተኛው የአእላፋት ዝማሬ ባለፈው ዓመት በልደት ዋዜማ ተካሔደ ። በአዘጋጆቹ እና በተሳታፊዎቹ ዘንድ ይህ ሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው ዙር በላይ ያማረ እና የሠመረ ሆኖ ተቆጥሯል ። በጠቅላላው ከምእመናን በኩል በተሳትፎም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ያገኘው ተቀባይነት ሌሎች ሁነቶች ሲሆኑ እንደምናየው በጅምር የሚቀር ሳይሆን እንደ ባህል የመተከል ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያመላክታል ። እንዲያውም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ብቻ ሳይወሰን ወደ ሌሎች ቦታዎችም እንዲሰፋ የሕዝብ ጥያቄ እና በአዘጋጆቹም በኩል እቅድ መኖሩ ይታወቃል ። ስለዚህ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ልክ እንደ ጥምቀት ሁሉ በሁሉም ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ (የአዘጋጆቹ አቅም በፈቀደው ልክ) የአእላፋት ዝማሬ የልደት በዓል መለያ ሆኖ እንዲካሔድ መጠበቅ እንችላለን ። ይህ ነገር በብዙዎች ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ጥቅም የሚሰጥ ሆኖ ይታያል ። በእነርሱ ዐይን ይህ ሁነት ቤተ ክርስቲያን በብዙዎች ዘንድ እንድትታወቅ ያደርጋል ። ብዙዎች በዓሉን አስመልክተው ከሚሔዱባቸው የማይገቡ ዓውዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ከማድረጉ ባሻገር ፥ በቤተ ክርስቲያን ሱታፌ ያላቸውንም በሚስብ እና በሚገባቸው መልኩ ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ እንዲያውቋት ያስችላቸዋል ። ስለዚህም የሌሉትን በመጥራት ፥ ያሉትንም በማጽናት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን እንድትዋጅ የሚያስችላት መሣሪያ ነው ፤ ከእርሷ ዘንድ ወደ ክሕደት እና ወደ ኑፋቄ የፈለሰውን ፥ ወይም በስም ክርስቲያን ሆኖ እና ማዕተብ አስሮ ሳለ በምድራዊ ተድላ ባሕር የሰጠመውን ወጣት ወደ ራሷ የምትስብበት መረብ ነው ። ነገር ግን ከኖረው የቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ አንጻር ከመረመርነው ፥ ይህ ሁነት

Read More »
Emmaus Posts
ኤልያስ ገብረ ሥላሴ

መከራ ፣ እከይ እና ክርስትና

መከራ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ድንገተኛ የሆነ ክስተት አይደለም ። ፍቅር በሆነው እግዚአብሔር ለጥቅማችን የሚፈቀድ የእርምት መንገድ ነው እንጂ ። በየዘመኑ ቤተክርስቲያን በወቅታዊ ሁነቶች እንድትወጠር እና መሠረታዊ ነገሮች ትኩረት እንዳያገኙ የሚቀርብ ፈተና አለ ። ሰበር ዜናዎች ፣ ወቅታዊ አጀንዳዎች ፣ አከራካሪ ጉዳዮች ወዘተ ከመነኩሴ መቁጠሪያ በላይ በሚሽከረከሩበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው ። እነዚህ ሁነቶች ትኩረታችንን ይወስዱትና ሳይታወቀን መሠረታዊ ከሆኑትና ዘለዓለማዊነታችንን ከሚበይኑት ጉዳዮች ወጥተን ምድራዊና እዚሁ ቀሪ በሆኑ ጉዳዮች ተወጥረን እንገኛለን ። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁኔታ በቤተክርስቲያንን መምህራን እና “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ላይ እጅግ በርትቶ የሚታይ መሆኑ እና በቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እና መድረኮች ሳይቀር ሰፊውን ሰዓት መያዙ ነው ። የቤተክርስቲያን ተልእኮ ስለ ክርስቶስ ምስክር መሆን ነው ። መሠረታዊ ካልሆኑት ሁነቶች ወጥተን ወደዚህ ዋነኛ ተልእኮአችን እንድንመለስ ተዋሥኦ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ። ይህ በምእመናን ፥ በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲን አገልጋዮች ፥ ዘንድ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው ። የሁነቶችን መሠረት መመርመርና ትክክለኛ ባሕርያቸውን መረዳት ያሻል ። ሁነቶቹ ችግሮች የሆኑ እንደሆነ ሥር ነቀል መፍትሔ ማሰብ የሚቻለው ፥ መልካም አጋጣሚዎችም ከሆኑ በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ ልናውላቸው የምንችለው የሁነቶቹን መሠረት በጥልቀት መረዳት ከቻልን ነው ። በመቀጠልም ተከትለው ሊደረጉ ስለሚገቡ ነገሮች መወያየት ከተቻለ ብቻ ነው ። ካልሆነ አሁን እየሆነ እንዳለው የወቅታዊ አጀንዳዎች አሳዳጅ ብቻ ሆነን ነው የምንቀረው ። በተለይ ዘመናችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ስለሆነ በዚህ

Read More »
Emmaus Posts
መሐሪ ዘመልአክ

ከእውነት አልባነት ጋር የሚካሔድ ሙግት

(‘ሐሳቦች መዘዝ አላቸው’ በሚል ርእስ በኤማሁስ መጽሔት ቅጽ 1 ፣ ቁጥር 1 በወጣው ጽሑፍ ላይ የተጻፈ አስተያየት) በመሐሪ ዘመልአክ (PhD) ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመታት በፊት የእጓለ ገብረ ዮሐንስ ‘የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ’ ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበብኹ በኋላ ጸሐፊውን ከዚያ በፊት አለማወቄ ገርሞኝ እንደነበር አስታውሳለኹ ። ማን ናቸው ? እንዴት እስከዛሬ ድረስ ስለእርሳቸው ሳልሰማ ቀረኹ ? ለምን ? ይኼ በ1956 ዓ.ም. የታተመ የሬድዮ ንግግር ከኾነ መጽሐፍ ለመጻፍ ብለው ተነሥተው ቢጽፉ ኖሮ ምን ሊጽፉ ነበረ ? ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎች ጭንቅላቴ ውስጥ ተመላልሰዋል ።[1] በኋላ ፈላስፋው ኦርቶዶክሳዊ አማኝ ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተማሪና መምህር እንደነበሩ ስሰማ በመጽሐፉ ውስጥ ያየሁት የሐሳብ ጥልቀት በዘመኑ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልሒቃን ዘንድ የነበረው ተዋሥኦ ሊደርስ ይንጠራራበት የነበረውን ልክ የጠቆመኝ መሰለኝ ። ከዚያ በኋላ ያ የተዋሥኦ ልሕቀት የት ገባ ? እንዴት ድርቅና የተጫነው ተዋሥኦ ዋጠው ? እንዴት ኦርቶዶክሳዊነትን ከአመክንዮ የተፋታ እና አመክንዮን የሚፈራ ጭፍን እምነት የሚያስመስሉ የፎክሎር ሰባኪዎች ተፈለፈሉብን ?  የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህን ለመኾን የሚጠየቀው መስፈርት ስለምን ድፍረት የለበሰ አላዋቂነት መሰለ ? በሚዲያ ላይ ሲናገሩ በአላዋቂነታቸው አንገታችንን የማያስደፉን ካህናት ስለምን ቁጥራቸው አልበረክት አለን ? ኦርቶዶክሳዊነት ችግርን እና ጭንቀትን ለማረሳሳት የተጠመቀ ዕፀ-ዝንጋዔ (‘opium of the masses’) እስኪመስል ድረስ በኦርቶዶክሳዊነት ስም የገነነው ተዋሥኦ ለምን አላዋቂነት ተጫነው ? ቤተ ክርስቲያን ሲባል ከስሜታዊ ሙጥኝታ (sentimental attachment) ባለፈ ለሰው ልጅ ህልውናዊ ጥያቄ የተሰጠ ከሞት ፍርኃት

Read More »
Emmaus Posts
ኤማሁስ

የኤማሁስ መንገድ

መጽሔቷን ለማግኘት ይህን ይጫኑ . . . የዘመናችን ተዋሥኦ በይዘቱም ሆነ በመንገዶቹ በግልብነት በእጅጉ የተጠቃ ነው ። ‘በይዘቱ እንዴት ?’ቢባል ሁነቶች ላይ ያተኮረ እና ወቅታዊነትን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ። አንድም አቋም ከመያዝና ጎራ ከፍሎ ከመናቆር ባለፈ የእውነት የመማር እና የማሰላሰል ጉጉት የማይታይበት በመሆኑ ። በዚህ ተዋሥኦ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሣት እና ከሁነቶቹ የሚሻገር እና ሐሳባዊ የሆነ ትንተና ለማካሔድ መሞከር ትኩረት ያስነሣል ፤ ሲብስም አጉል እንደመራቀቅ ይታያል ። የሚካሄድበት ከባቢ እና ዘመን ደግሞ ሌላ ግልብነት ደርቦለታል ። በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት ፣ ከዘመናዊነትና ከቴክኖሎጂ መራቀቅ ጋር ተያይዞ ሕዝባዊ ተዋሥኦ በጠቅላላው ስለቱን እና ርቀቱን እንዲያጣ ሆኗል ። የሚነበብም ሆነ የሚታይ ወይም የሚደመጥ ነገር አጭር መሆን አለበት ። ነገር ግን ጠቃሚና ወሳኝ ርእሶች እንዲህ ባለ መንገድ ሊስተናገዱ አይችሉም ። የሚያጠግብ ፍሬ ከሌለበት የተመልካቹ እና የአንባቢው ብዛት ምን ጥቅም ይኖረዋል ? እንዲህ ባለው ከባቢ ውስጥ ሁነቶችን ከሁነትነታቸው እና ከሚያመጡት ወቅታዊ ውጤት በተሻገረ መልኩ ለመመልከት እንቸገራለን ። ቀድሞውኑም (እይታችን ከመጥበቡ የተነሣ) ጠባብ አድርገን የቀረጽነውን አጀንዳ በምንገልጽበት መንገድ የበለጠ እናጠብበዋለን ። ነገር ግን ሁነቶችን እና ሒደቶችን ከመሠረታቸው መመርመራችን እና የምናቀርባቸው መፍትሔዎችም እንዲሁ የማይናወጥ መሠረት ያላቸው መሆናቸው አስፈላጊ ከሆነ ተዋሥኦውም እንዲሁ የጠለቀ እና የረቀቀ መሆን አለበት ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ፣ ማንበብ ፣ ማጠናቀር ፣ መወያየት ፣ መሟገት እና እንዲህ ካለው ሒደት

Read More »
Emmaus Posts
በርናባስ ሽፈራው

ክፍል ፭ ፡ ወደ ርስታችን ያልተመለስንበት ኢዮቤልዩ

ሩሲያዊው ደራሲ ፌዮዶር ዶስቶየቭስኪ በ1860ዎቹ አውሮፓን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኝ የታዘበውን በዘገበበት ማስታወሻው የለንደን ድሆች ቅዳሜ ማታን እንዴት ባለ መንገድ እንደሚያሳልፉ ይነግረናል ። በቅድሚያ ሌሊቱን በሙሉ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ጭምር ደስታ ፈጽሞ በተለየው ፣ ድብርት በተጫነው መንፈስ አኳዃን ሲበሉ እና ሲጠጡ ፣ ከሕይወታቸው መራራነት ለማምለጥ ፣ ራሳቸውን ፍጹም ለማደንዘዝ በሙሉ ጥምብዝ እስኪሉ እንደሚሰክሩ መስማቱን ይዘግባል ። ሳምንቱን ሙሉ ሠርተው የቋጠሯትን ገንዘብ ቅዳሜ ሌሊት እንዲህ ይበትኗታል ። አስከትሎም እንዲህ ባለው አንድ ምሽት እሱ ራሱ በመንደራቸው ውስጥ ሲያልፍ የታዘበውን እና የተሰማውን እንደሚከተለው ይመሰክራል ። “One such night – it was getting on for two o’clock in the morning – I lost my way and for a long time trudged the streets in the midst of a vast crowd of gloomy people, asking my way almost by gestures, because I do not know a word of English. I found my way, but the impression of what I had seen tormented me for three days afterwards. The populace is much the same anywhere, but there all was so vast, so vivid that you almost physically felt things which up till then you had only imagined. In London, you no longer see the populace. Instead, you see a loss of sensibility, systematic, resigned and

Read More »