መከራ በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ድንገተኛ የሆነ ክስተት አይደለም ። ፍቅር በሆነው እግዚአብሔር ለጥቅማችን የሚፈቀድ የእርምት መንገድ ነው እንጂ ። በየዘመኑ ቤተክርስቲያን በወቅታዊ ሁነቶች እንድትወጠር እና መሠረታዊ ነገሮች ትኩረት እንዳያገኙ የሚቀርብ ፈተና አለ ። ሰበር ዜናዎች ፣ ወቅታዊ አጀንዳዎች ፣ አከራካሪ ጉዳዮች ወዘተ ከመነኩሴ መቁጠሪያ በላይ በሚሽከረከሩበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው ። እነዚህ ሁነቶች ትኩረታችንን ይወስዱትና ሳይታወቀን መሠረታዊ ከሆኑትና ዘለዓለማዊነታችንን ከሚበይኑት ጉዳዮች ወጥተን ምድራዊና እዚሁ ቀሪ በሆኑ ጉዳዮች ተወጥረን እንገኛለን ። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ሁኔታ በቤተክርስቲያንን መምህራን እና “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ላይ እጅግ በርትቶ የሚታይ መሆኑ እና በቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እና መድረኮች ሳይቀር ሰፊውን ሰዓት መያዙ ነው ።
የቤተክርስቲያን ተልእኮ ስለ ክርስቶስ ምስክር መሆን ነው ። መሠረታዊ ካልሆኑት ሁነቶች ወጥተን ወደዚህ ዋነኛ ተልእኮአችን እንድንመለስ ተዋሥኦ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ። ይህ በምእመናን ፥ በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲን አገልጋዮች ፥ ዘንድ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው ። የሁነቶችን መሠረት መመርመርና ትክክለኛ ባሕርያቸውን መረዳት ያሻል ። ሁነቶቹ ችግሮች የሆኑ እንደሆነ ሥር ነቀል መፍትሔ ማሰብ የሚቻለው ፥ መልካም አጋጣሚዎችም ከሆኑ በትክክለኛው መንገድ ጥቅም ላይ ልናውላቸው የምንችለው የሁነቶቹን መሠረት በጥልቀት መረዳት ከቻልን ነው ። በመቀጠልም ተከትለው ሊደረጉ ስለሚገቡ ነገሮች መወያየት ከተቻለ ብቻ ነው ። ካልሆነ አሁን እየሆነ እንዳለው የወቅታዊ አጀንዳዎች አሳዳጅ ብቻ ሆነን ነው የምንቀረው ።
በተለይ ዘመናችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ስለሆነ በዚህ መደላድል ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ሁነት ተኮር ልጥፎች ፣ ውይይቶችና ክርክሮች ወደ መሠረታዊ ነገሮች እንዲያተኩሩ እና በቶሎ ፈር እንዲይዙ ካልተደረገ በብዙኃኑ ዘንድ ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋ ከዚህ የዘለለ እንዳልሆነ ተደርጋ እንድትታሰብ እና ሰማያዊነቷ እንዲዘነጋ ያደርጋል ። በዚህ ረገድ ኤማሁስ ፖድካስት እና መጽሔት ፈር ቀዳጅ ሆነው ብቅ ብለዋል ። በዚህ አጋጣሚ ኤማሁስ ፖድካስትና መጽሔትን እንድትከታተሉ ለሌሎችም እንድታጋሩ እጋብዛለሁ ።
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥያቄ የሚፈጥሩብን ፣ ለመረዳት የሚያስቸግሩንና ስለ እግዚአብሔር መልካምነት ካለን ዕውቀት ጋር የሚጋጩ የሚመስሉ አንዳንድ ጥቅሶች አሉ ። “ብርሃንን ሠራሁ ፤ ጨለማውን ፈጠርሁ ። ደኅንነትን እሠራለሁ ፤ ክፋትንም እፈጥራለሁ ። እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ።” የሚለው በትንቢተ ኢሳይያስ ያለው ኃይለ ቃል ከነዚህ ጥቅሶች ውስጥ አንዱ ነው ። “ክፋትን እፈጥራለሁ” በሚለው መጣጥፉ ወንድማችን ብንያም የዚህን ከባድ ጥቅስ ትርጉም በቤተክርስቲያን ህያው በሆነው የአባቶች ትምህርት በኩል እንድንረዳው ይጋብዘናል ። ጽሑፉ የጥቅሱን ትርጉም በማስረዳት ውስጥ ስለ መልካም (በጎ) ፣ ክፋት (እከይ) እና መለኮታዊ መግቦት (Divine providence) በቤተክርስቲያን አባቶች ትምህርት መነሻነት ጥልቅ የሆነ ነገረ መለኮታዊ ትንተና የተሰጠበት ነው ። በየዘመኑ አማኞች ‘ክፋት ከየት መጣ ? እግዚአብሔር ለምን ይፈቅደዋል ? ከእግዚአብሔር መልካምነትስ ጋር እንዴት አብሮ ይሄዳል ?’ በሚሉና በመሰል ጥያቄዎች ይፈተናሉ ። ይህ መጣጥፍ ለነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የተሰጠበት ነው ።
ጽሑፉ የሚጀምረው ክፋት እንደ ተመልካቹ ነው የሚለውን የሞራላዊ (ግብረ ገብ) አንጻራዊነትን (Moral Relativism) ዕሳቤ ስሕተትነት በጥቂቱ በመጠቆም ነው ። ይህንን ዕሳቤ ከሚያንጸባርቀው ‘ክፋትን ስናየው እናውቀዋለን’ ከሚለው አባባል በመነሣት አንባቢውን ከግላዊ የሞራል (Moral Subjectivism) አረዳድ አውጥቶ ወደ ገሀዳዊ የሞራል (Moral Objectivism) አረዳድ ይወስደዋል ። በዚህም ጉዳዩን ከግላዊ አተያይ (Personal Opinion) በማሻገር መልካምን መልካም፤ ክፉንም ክፉ የሚያሰኙት ወይም የሚያደርጉት ነገሮች ምንድናቸው? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ይመልሳል ። የፈጠረው ነገር ሁሉ መልካም እንደሆነ የተመለከተ እግዚአብሔር “ክፋትን እፈጥራለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን ለመረዳት ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ የግድ ነው ። ብንያም ይህንን የሚያደርገው ፈላስፋው ሶቅራጥስ ዩቲፍሮ ለሚባል ወዳጁ ያቀረበለትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ሞራል (ግብረ ገብ) የእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነገር ነው ? ወይስ ከእግዚአብሔር ውጪ ያለ በራሱ ቀዋሚ የሆነ ነገር ነው? የሚል ጥያቄ በማንሣት እና የዚህን ጥያቄ ምላሽ በማብራራት ነው ።
የመጣጥፉ ጠንካራ ጎን ይህን ጥያቄ የቤተክርስቲያን አባቶች እንዲመልሱት ማድረጉ ነው ። ብንያም ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ ፍለጋ የተጓዘው ወደ ቀደሙ አባቶች ወደነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ፣ ዲዮናስዮስ ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እና ከቅርብ ዘመን የነገረ መለኮት ሊቃውንት ወደነ ዱሚትሩ ስታኒሎይ ፣ ክርስቶስ ያናራስ ፣ ጆርጀስ ፍሎሮቭስኪ እና ዴቪድ ቤንትሌይ ሀርት ነው ። በዚህም ኦርቶዶክሳዊነት ‘በከመ መሀሩነ አበው – አባቶች እዳስተማሩን’ ማለት እንደመሆኑ አባቶችን እንዲሁ ለመጥቀስ ያህል ሳይሆን እያንዳንዱ የተጠቀሰው ትምህርታቸው ጽሑፉን አንድ እርምጃ እያስጓዘ በስተመጨረሻም ልክ (Sound) ወደ ሆነው የጽሑፉ መነሻ ጥቅስ መረዳት የሚያደርስ ነው ። በአጭሩ ጽሑፉ መነሻ እና መድረሻ ያደረገው የቤተክርስቲያን አባቶችን ነው ።
የመጣጥፉ የጀርባ አጥንት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ስለ ክፋት ምንነት ያስተማረው ትምህርት ነው ። እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አስተምህሮ ክፋት የበጎነት አለመኖር ወይም መታጣት ሲሆን ክፋት በራሱ ህላዌ ወይም ምንነት የሌለው ነው ። ስለዚህ ክፋት በእግዚአብሔር የተፈጠረ ሳይሆን የበጎነት ወይም መልካምነት አለመኖር ነው ። ከዚህ በመነሣት ብንያም ክፋት የምንለው ፍጡር ለባሕርይው የማይስማማ እንቅስቃሴ ማድረጉን መሆኑን ያወሳል ። የዲዮናስዮስ ዐሳብም ተጠቅልሎ ክፋት በራሱ ህልው ያልሆነ ነገር ግን ጥገኛ በመሆን ሰውነትን በሚጎዳ በሽታ ተመስሎ ቀርቧል ። ፍሎሮቭስኪም ክፋት ነጻ ፈቃድ ያላቸው ፍጥረቶች (መላእክት እና ሰዎች) በምርጫቸው ከእግዚአብሔር መቃረናቸው የሚያመጣው ውጤት ነው በማለት ይህንኑ ዐሳብ ያጠናክረዋል ። “ክፋት የመንፈስ ክሂላት ወደተሰጣቸው መዳረሻ ያይደለ ወደ ሌላ ነገር የሚያደርጉት ኢ ምክንያታዊ እንቅስቃሴ ነው” የሚለው የስታኒሎይ አረዳድ ደግሞ የጽሑፉን ጠቅላላ ዐሳብ ከነጻነት እና ሐላፊነት ጎዳና አንጻር የሚያስር ነው ። ምክንያቱም ሰው የመረጠውን እንቅስቃሴ የማድረግ ነጻነት እንዳለው ሁሉ ፥ ላደረገው እንቅስቃሴም ሓላፊነትን የመውሰድ ግዴታ አለበትና ነው ። በነጻነቱ መርጦ ለተፈጥሮው የማይስማማ ኢ-ምክንያታዊ እንቅስቃሴ ባደረገ ቁጥር ክፋት ይወለዳል ፤ የዚህም ክፋት ባለቤትነት (ሐላፊነት) ደግሞ የራሱ ነው ። በአጠቃላይ መልካም ወይም በጎ የምንለው ከእግዚአብሔር የተገኘውን እና የእርሱ ፈቃድ የሆነውን ነገር ሁሉ ነው ። ክፋት ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው ። ስለዚህ የክፋት ምንጩ ኃጢአት ነው ፤ ምክንያቱም ኃጢአት ከእግዚአብሔር መቃረን ነውና ።
ብንያም በመቀጠል ‘በሞራላዊ እኩይ’ እና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‘እኩይ ሊባሉ የማይገባቸው ፥ ነገር ግን እኩይ የምንላቸው’ በሚላቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት በጥንቃቄ ያስረዳል ። ቅዱሱ እኩይ ሊባሉ የሚገባቸው የሚለው ሞራላዊ የሆኑትን እንደ ዝሙት እና ፍቅረ ንዋይ ያሉ ነገሮችን ሲሆን ፤ እኩይ ሊባሉ የማይገባቸው ነገር ግን እንደዛ እያልን የምንጠራቸው የሚላቸው ደግሞ እንደ ረኃብ ፣ ወረርሽኝ ፣ ሞት ፣ በሽታ ያሉትን ነው ። ብንያም ቅዱሱን መነሻ በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ በአንዳንድ ቦታ እነዚህን እኩይ ሊባሉ የማይገባቸው ነገሮች እኩይ ሲላቸው ቢገኝም በሞራላዊ ዐውድ ማለቱ አይደለም ይለናል ። በኢሳይያስ ትንቢትም ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለው በዚሁ አግባብ ነው ። ለዚህም በተመሳሳይ መንገድ ያቀረበው አመክንዮ ‘እነዚህ ነገሮች ክፉ (እኩይ) ቢሆኑ ኖሮ ትዕቢታችንን በመገሠፅ ፣ ስንፍናችንን በማባረር ወደ መነሣሣት እየመሩን እና ትኩረታችንን ወደ ሚገባው ቦታ እየሳቡልን የመልካም ነገር መገኛ ባልሆኑልን ነበር ።’ የሚል ነው ። ይህ እጅግ መሠረታዊ የሆነ ጉዳይ ነው ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ክፋትን እንዳልፈጠረ ከማስረገጡ በተጨማሪ ክፉ ሳይሆኑ ክፉ እያልን በምንጠራቸው ነገር ግን የእግዚአብሔር የመግቦቱ መገለጫ በሆኑ ነገሮች እና ክፉ የሚለው መጠሪያ በሚገባው በሞራላዊ ክፋት መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ ነው ።
ተሰናስሎውን በጠበቀ መንገድ ይህንን መደላድል ከፈጠረ በኋላ ነው ብንያም የተነሣበትን የኢሳይያስን ትንቢት ቃል ወደ ማብራራት የሚገባው ። እግዚአብሔር “ክፋትን እፈጥራለሁ” ሲል ክፋት የተባለው ሞራላዊ እኩይ ሳይሆን የመግቦቱ አካል የሆነው መቅሰፍት ነው ። ለዚህም ማሳያ እንዲሆን የአይሁድ ሊቃውንት ይህንን የትንቢት ክፍል ሲተረጉሙ ጨለማን ‘የብርሃን አለመኖር’ ፥ ክፋትንም ‘የሰላም አለመኖር’ ብለው እንደፈቱት ያነሣል ። ስለዚህ ‘ክፋትን እፈጥራለሁ’ ማለቱ (የሰላም አለመኖር) በፋርስና በባቢሎን መካከል ጦርነት አመጣለሁ ማለቱ ሲሆን ‹ደኅንነትን እሠራለሁ› ማለቱ ደግሞ የፋርሱን ንጉሥ ቂሮስን እንደሚያበረታው መናገሩ ነው ብለው መተርጎማቸውን ያነሣል ። ቅን ለሆኑት ብርሃንን ለክፉዎች ደግሞ ጨለማን እንደሚከፍል በማውሳት ለዚህ ማሳያ በቅዳሴ ማርያም ኅብስቱ እና ወይኑ እንደተቀባዮቹ ሁኔታ ውጤቱ የተለያየ መሆኑ የተገለጠበትን ከፍለ ንባብ ያነሣል ። ከዚህ በመቀጠል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን መነሻ በማድረግ በኢሳይያስ ትንቢት ክፋት የተባለው ከሰው ፈቃድ የሚመነጨው ክፋት ሳይሆን እግዚአብሔር ከመግቦት የተነሣ ለእርምት ወይም ለማስተማሪያነት የሚያመጣቸው መቅሰፍቶችን መሆኑን እና የጥቅሱ ትርጉምም ይኸው መሆኑን ያስረግጣል ።
ብንያም ጽሑፉን የሚጠቀልለው ይህንን ከላይ ያብራራውን እውነት በተግባር የቀመሰውን ጻድቁን ኢዮብን በማንሣት ነው ።ኢዮብ ከሰይጣን በሆኑ ብዙ ፈተናዎች ተፈትኗል ። እነዚህ ፈተናዎች ከሰይጣን ይሁኑ እንጂ ኢዮብ ይፈተንባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃዱን የሰጠባቸው ናቸው ። ይህም የኢዮብ እምነት ይፈተን ዘንድ ነው ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከመግቦቱ የተነሣ ኢዮብን በፈተና ውስጥ ሊያስተምረው ይፈተንባቸው ዘንድ ፈቃዱን የሰጠባቸው መቅሰፍቶች ናቸው ። እነዚህ በራሳቸው ክፉ አይደሉም ፤ ምክንያቱም ኢዮብ ቢያገኝም ቢያጣም በጽድቅ ሕይወት መጽናት እንዳለበት ይማርበት ዘንድ የመጡ ፈተናዎች ናቸውና ። ክፋት ይመነጭ የነበረው ኢዮብ በፈተናው ወድቆ እግዚአብሔርን ቢበድል ፤ ኃጢአት ቢሠራ ነበር ። ምክንያቱም የክፋት ምንጩ ኃጢአት ነውና ። ስለዚህ ጥቅሱ ላይ እግዚአብሔር እፈጥረዋለሁ ያለው ክፋት ሞራላዊ የሆነውን እና ነጻ ፈቃድ ካላቸው ፍጥረታት የሚመነጨውን ክፋት ሳይሆን ከመግቦቱ ስለ ጥቅማችን የሚያመጣቸው መቅሰፍቶችን ነው ።
መጣጥፉ መነሻው ላደረገው ጥቅስ ምላሽ ከመስጠትም በዘለለ ኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሰብእን (ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ምን እንደሆነ እና ከዛ የተቃረነ እንቅስቃሴም ውጤቱ ምን እንደሆነ እግረ መንገድ የተብራራበት ነውና) እና የእግዚአብሔርን እውነተኛ ኖላዊነት ያብራራ ነው ። ክፋት የሰው ፈቃድ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ሲፃረር የሚፈጠር ነው ። መቅሰፍቶችም ለንስሐ የሚያነቁ ወይም እምነት የሚፈተንባቸው መንገዶች ናቸው እንጂ በባሕርያቸው ክፉዎች አይደሉም ። ከዚህ በመጀመሪያ የምንረዳው ሰው ‘ሰው’ ሆኖ እንዲኖር እና የተፈጠረበትም ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ፈቃዱን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር አስማምቶ መኖር እንዳለበት ሲሆን ሁለተኛው እግዚአብሔር ክፉ በሚመስሉ መግቦቶቹ ውስጥ ስንኳ መልካም እንደሆነ ነው ።
እንደማጠቃለያ ይህ ጽሑፍ ተቃርኖ ያለበት የሚመስል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተብራራበት ብቻ ሳይሆን አንባቢውን ኦርቶዶክሳዊ ወደ ሆነው እይታ ፥ ይኸውም እግዚአብሔር ጨለማ የሌለበት ብርሃን ፥ ክፋት የሌለበት መልካም መሆኑንና በሱ መግቦት የሚፈቀድ ፈተና ሁሉ የኛን ፈቃድ ከእርሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ስለ ጥቅማችን የሚፈቅደው መሆኑን ያብራራ ነው ማለት ይቻላል ። መጣጥፉን እንድታነቡት ለሌሎችም እንድታጋሩት በድጋሚ አሳስባለሁ ። መልካም ጊዜ!






እናመሰግናለን 🙏