መምህር ያረጋል ለዘነበ ወላ የሰጠውን መልስ ተከትሎ በኤማሁስ ፕሬስ ጸሐፍት በኩል የቀረበው ትችት አግባብ አለመሆኑን የሚገልጥ አንድ ጽሑፍ አጋርቶናል። ጽሑፉም እዚሁ ገጽ ላይ የወጣ ስለሆነ ብዙ ሰው ያነበበው ይመስለኛል። ያረጋል በዚህ ጽሑፉ ሁለት ነገሮችን ማስተላለፍ የፈለገ ነው የሚመስለኝ። የመጀመሪያው ለዘነበ ወላ የሰጠው መልስ ፈጽሞ በ’reductionism’ የሚከሰስ አለመሆኑን ማሳየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጸሐፍቱ እንዲያው እሱን እንንቀፈው ብለው ካልሆነ በስተቀር የጻፉትን የሚያጽፍ ምክንያት ከእርሱ ጽሑፍ ውስጥ የማያገኙ መሆኑን መጠቆም የፈለገ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
በርግጥ በዚህ ጽሑፍ እኔ ማተኮር የፈለግሁት ሁለተኛው ላይ ቢሆንም፣ ከ“reductionism” ጋር በተያያዘ ስለተነሣው የመጀመሪያው ጉዳይ ግን ትንሽ ነገር ልናገር። ‘reductionism’ (የራሱን የያረጋልን ትርጉም ልጠቀምና – ክርስትናን ወደ ምድራዊ እሳቤና መለኪያ ዝቅ ማድረግ) የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ከልዕልናው አውርዶ ጊዜያዊ ለሆኑ ሌሎች የኑሮ ዘይቤዎች ተገዢ የሚያደረግ አደገኛ መንገድ ነው። በመሆኑም በነገረ መለኮት ሊቃውንት ደረጃ በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያሉ ውይይቶች መደረግ ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል። በኤማሁስም በኩል፣ ይኼ ርእሰ ጉዳይ ሲነሣ፣ የኤርሚያስ እና የበርናባስ ጽሑፍ የመጀመሪያው አይደለም። ያረጋል ከጻፈው ጽሑፍ ጋር ሳይገናኝ፣ ከአሁን በፊት በሠራናቸው ፖድካስቶች ማሳነስን (reductionism) እንደ አንድ አደገኛ ዝንባሌ ስናነሣ እንደነበር ሲከታተሉን የነበሩ ሰዎች የሚያስታውሱ ይመስለኛል። ነገር ግን ስለነገሩ ምንነትም ሆነ ስላለው አደጋ ገና እንዳልተግባባን እና በዚሁ ጉዳይ ከዚህም በላይ ገፋ አድርገን መነጋገር የሚገባን ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ይኼው የያረጋል መልስ ይመስለኛል። ያረጋል ጽሑፉን ለመከላከል የቅዱሳት መጻሕፍትን አቀራረብ ያነሣበት አግባብ፣ የቀረበበትን ትችት “ስለ አንድ ጉዳይ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ እንዲገለጥ” ከመፈለግ ጋር ያነጻጻረበት መንገድ፣ ገፋ ሲልም መልስ የሰጠበትን መንገድ “ዐለምን ከመዋጀት” ጋር ያገናኘበት ሂደት፣ እውነቱን ለመናገር፣ አሳብ ለአሳብ እንዳልተገናኘን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን በርእሰ ጉዳዩ ላይ በቂ ጊዜ ወስደን መነጋገር እንዳለብን የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው። ስለዚህ እንደጀመርን ውይይቱን መግፋት እንዳለብን ይሰማኛል። በዚሁ መሠረት አሳቡን የበለጠ ለውይይት ክፍት ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ኤርሚያስ እና በርናባስ በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ሁለተኛ ጽሑፋቸውን በዚሁ ገጽ በቅርቡ እንደሚያቀርቡ እየጠቆምሁ፣ እኔም የማሳነሱን (reductionism) ነገር ለእነርሱ ላቆየዉና ዛሬ ማተኮር ወደፈለግሁበት ሁለተኛው ነገሬ ልግባ።
መምህር ያረጋል በጽሑፉ መጨረሻ አካባቢ፣ የነገሮቹ ሁሉ መነሻ የሆነው የዘነበ ወላ ነቀፌታ ወደ ጎን ተብሎ፣ ፈጽሞ የእሱ አሳብ ወዳልነበረው ርእሰ ጉዳይ ጽሑፉ መወሰዱ ቅር እንዳሰኘው ተናግሯል። በርግጥ ይኼንኑ ስሜት፣ ሲሰጡ በነበሩ ሌሎች አስተያየቶች ውስጥም አስተውለናል። ለማስታወስ ያህል ግን፣ በኤማሁስ በኩል የቀረበው ጽሑፍ ምንም እንኳን ዋና ትኩረት አድርጎት የነበረው ጽንሰ አሳብ ላይ ብዙ ጊዜ የወሰደ ቢሆንም፣ የዘነበን ንግግር ግን ሙሉ ለሙሉ በዝምታ ያለፈ አልነበረም፤ በተናጋሪው ሰው ደረጃ እና ልክ በአጭሩ አሳብ ተሰጥቶበታል። ከዚያ በላይ የዘነበ ንግግር ላይ ሰፊ ትንተና ለማቅረብ የሚያስችል ቁም ነገር ነበር ብለን ግን አናምንም። የዘነበ ዓይነቱ ትችት ስለ ቤተ ክርስቲያን ሩቅ እና ከላይ ከላይ የሆነ ግንዛቤ ካላቸው ሰዎች አንደበት የሚጠፋ አይደለም። ነገሩ ከአንድ ከዘነበ ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑን ያረጋልም መጠቆሙም ትክክል ነው። ስለዚህ እኛ የመረጥነው መንገድ ውይይቱን በጽንሰ አሳብ ደረጃ ማድረግን ነበር። በኤማሁስ በኩል የቀረበው ጽሑፍ ፍሬ ነገር በቀጥታ ቢነገር ፣ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለተሰነዘረ የሐሰት ክስ የምንሰጠው መልስ፣ ለክስርትና እምነት መሠረታውያን እውነቶች የተገዛ መሆኑን እና እንደ ዘነበ የተናጋሪውንም ይሁን ሌሎች ጉዳዩን የሚከታተሉ ሰዎች ግንዛቤ እና አመለካከት ላይ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንዲቀርብ የታሰበበት መሆኑን መፈተሽ አለብን የሚል ነው። የያረጋልን ጽሑፍ ከ’reductionism’ አንጻር ማየት የመፈለጉ ምክንያትም የመጣው ከዚሁ መሠረታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነበር። ያረጋል እንደመሰለው፣ እሱ ማንሣት የፈለገውን ነገር ወደ ጎን ብለን፣ ግንኙነት የሌለው ነገር (እሱ እንዳለው ‘ያልበላን ማከክ’) በማንሣት ‘ሌላ reductionist’ እየሆንን ሳይሆን፣ ቢያንስ የያረጋል ጽሑፍ በዚህ በኩል ክፍተት ሊኖርበት አይገባም ነበር ከሚል ወንድማዊ ቅናት የመነጨ መሆኑ ቢታሰብ ደስ ይለኛል።
ይኼን ስንል ግን፣ ቤተ ክርስቲያን በውስጥም በውጪም በፈተና ተወጥራ ባለችበት በዚህ ወቅት እንደሚኖር ሰው፣ የዘነበ ዓይነቱ ትችት ሊፈጥረው ከሚችለው ስሜት ነጻ ሆነን አይደለም። ‘ዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ’ እንደሚባለው፣ ማዘንንም፣ መፍታትንም በአንድ ላይ እንድናከናውን ግድ ያለ ዘመን ላይ ስለወደቅን፣ በትዕግስት እና በጥንቃቄ የመሥራትን ሕመም ከመሸከም ውጪ አማራጭ የለንም ብለን ስለምናስብ እንጂ። ይኼንን እንድናደርግ የሚያደርገን ደግሞ፣ የቆምንበት የክርስትና እውነት ነው። ስለዚህ ዘነበ ወላ “ዝም በል” የተባለበት መንገድ ትክክል ነው፣ አይደለም? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገንም ሌላ ነገር ሳይሆን የቆምንበት ይኼው የራሳችን እውነት ነው። እውነቱን ለመናገር፣ ለያረጋል ይኼንን በጽንሰ አሳብ ደረጃ የሚነግሩት ሆኖ አይደለም፤ ነገር ግን እሱ ብቻ ሳይሆን የሁላችንንም ሚዛን የሚያስት ጫና ውስጥ ነውና እየኖርን ያለነው፣ ኃይላችንም አቅማችንም እውነታችን ላይ እንጂ ሌላ ቦታ ላይ የማይገኝ መሆኑ በስሜት እንዳይዘነጋ ለማሳሰብ ያህል ነው።
በርግጥ እዚህ ላይ ሳይነሣ መታለፍ የሌለበት፣ ከዘነበ ጋር የተያያዘው ሰሞንኛው ነገር ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ከዕቅበት እምነት ጋር በተያያዘ የምንሠራቸው ሥራዎች፣ በጫናው ምክንያት፣ ብዙ ጊዜ ሚዛናቸውን ይስታሉ። ብዙ ማሳያዎችን ማንሣት ይቻላል፤ ይኼ የእኔ ትዝብት ብቻም አይመስለኝም። ዝርዝሩን አቆይቼ መፍትሔ ወደምለው ስመጣ ግን፣ ዕቅበተ እምነትን መንገድ በሚያቋርጥ ሰው መመሰል የሚቻል ይመስለኛል። መንገድ የሚያቋርጥ ሰው በግራም በቀኝም ያለውን እንቅስቃሴ ዕያየ እንደሚሻገረው ሁሉ፣ ዕቅበተ እምነታችንም ሙሉ በሙሉ ፊቱን በግራ በኩል ወደ መጣው አደጋ አዙሮ ሳይሆን፣ በቀኝ በኩል የሚመክቱለት ወዳጆቹንም ዞር ብሎ ዕያየ ካልተሻገረ መንገዱ መሀል ከቀኝ በኩልም ሊመጣ በሚችል አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል ማሰብ ያለበት ይመስለኛል። እኛም ብንሆን፣ ወደ ቀኝ ዞር ብለን ያረጋልን ማየታችን ከዚሁ ከጥንቃቄ አንጻር እንጂ ‘ከትብብር ይልቅ ነቀፌታን የመምረጥ’ ፍላጎት በፍጹም አልነበረም።
በዚሁ ምክንያት፣ ያረጋል የኤርሚያስን እና የበርናባስን ጽሑፍ የነቀፋ እና የፍረጃ አድርጎ መውሰዱ ትክክል አይደለም። እንደ ኤማሁስ፣ የቤተ ክርስቲያንን ችግር መፍታት የምንችለው ጠንካራ እና ደፋር ጥያቄዎችን እያነሣን ለመነጋገር ፈቃዱ እና ተነሣሽነቱ እሰካለ ደረስ ነው የሚል እምነት እንዳለን በተደጋጋሚ እናነሣለን። በዚሁ መሠረት ለውይይት መቅረብ አለባቸው ብለን የምናስባቸውን ነገሮች ወደ ሕዝቡ ለማቅረብ እንሞክራለን። ለያረጋልም የተሰጠው መልስ በዚሁ አግባብ የቀረበ እና ለተመሳሳይ ዓላማ የተጻፈ ነው። እሱም የጻፈውን ነገር፣ የጻፈውን ያነበቡም ያነበቡትን ነገር መለስ ብለው እንዲያዩ፣ ግራ ቀኙን እንዲመረምሩ በማሰብ ለአንድ ዓላማ የተጻፈ እንጂ በፍጹም ለመነቃቀፍ የቀረበ ጽሑፍ አልነበረም። ይኼ ደግሞ ምቾት የመንሳት ነገር ቢኖረውም፣ የግድ መለመድ አለበት ብለን ግን እናምናለን። ከዚህ ውጪ ለችግሮቻችን መውጫ አለ ብለን አናስብምና። በዚሁ መልኩ መረዳት ቢቻል እላለሁ።






እግዚአብሔር ይስጥልኝ!!
-ቀጣዩን የተዋሥኦ ክፍል እጠብቃለሁ። ኤማሁስ ቤተሰብ በርቱ!
ቅንነትን መሠረት ያደረገ ትችት፥ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጥብቅና እቆማለሁ የሚል ማንም አገልጋይ ሊፈራውም ሆነ ሊሸሸው የማይገባ ነው። በመሆኑም፥ እያንዳንዱ አገልጋይ ራሱን ለእንደዚህ ዓይነት ትችት ዝግጁ ማድረግ አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ትችት ባለመለመዱ ብዙ ችግር እንዳጋጠመን አስባለሁ። ይህንኑ አካሄድ መከተሉ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሯችን ነጥሮ አንዲወጣ የራሱ ሚና ይጫወታል ብየ አምናለሁ።
ውድ የኤማሁስ ቤተ ሰብ በርቱ ቀጥሉበት እግዚአብሔር አምላክ አገልግሎታቹህ ያስፋ።
Great perspective and it’s very thoughtful.
Stay blessed
Guys watching some of ur videos u guys are very bold. But concerning u and Yaregal , u could have prepared concrete response to that fiction writer. ቤቱን አሮጌ ነዉ አትበለዉ።build a new house near by. ቤቱ ለራሱም ምስክር ለዛም ጉድለት ማሳያ ይሆናል። i sympathize with ur concern but he is an icon , ur battles decreases his influence.
እርግጠኛ መምህራችን ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ እንዲህ ያለውን መልካም ቅናት እንደሚደግፍ።እግዝአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን።ኤማሁስ podcast ደግሞ ንቁ በሆኑ ወጣት ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ በጣም እየተወደደ ነው በየ telegram group ማየው አስተያየት ይህንን ነው ሚያሳየው በርቱልን
I am glad this ‘conversation’ happened here. It is good to discuss ideas, opinions and understandings, so each can take note of what is happening. I think its good you have commented on Memhir Yaregal’s post and that he has responded to your criticism. And now you are responding again.
I believe this is the way to go, criticizing each others ideas and refining the way towards the same goal you are working to achive. (Which i belive is Saving Souls)