. . . የዘመናችን ተዋሥኦ በይዘቱም ሆነ በመንገዶቹ በግልብነት በእጅጉ የተጠቃ ነው ። ‘በይዘቱ እንዴት ?’ቢባል ሁነቶች ላይ ያተኮረ እና ወቅታዊነትን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ ። አንድም አቋም ከመያዝና ጎራ ከፍሎ ከመናቆር ባለፈ የእውነት የመማር እና የማሰላሰል ጉጉት የማይታይበት በመሆኑ ። በዚህ ተዋሥኦ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሣት እና ከሁነቶቹ የሚሻገር እና ሐሳባዊ የሆነ ትንተና ለማካሔድ መሞከር ትኩረት ያስነሣል ፤ ሲብስም አጉል እንደመራቀቅ ይታያል ።
የሚካሄድበት ከባቢ እና ዘመን ደግሞ ሌላ ግልብነት ደርቦለታል ። በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሀገራት ፣ ከዘመናዊነትና ከቴክኖሎጂ መራቀቅ ጋር ተያይዞ ሕዝባዊ ተዋሥኦ በጠቅላላው ስለቱን እና ርቀቱን እንዲያጣ ሆኗል ። የሚነበብም ሆነ የሚታይ ወይም የሚደመጥ ነገር አጭር መሆን አለበት ። ነገር ግን ጠቃሚና ወሳኝ ርእሶች እንዲህ ባለ መንገድ ሊስተናገዱ አይችሉም ። የሚያጠግብ ፍሬ ከሌለበት የተመልካቹ እና የአንባቢው ብዛት ምን ጥቅም ይኖረዋል ?
እንዲህ ባለው ከባቢ ውስጥ ሁነቶችን ከሁነትነታቸው እና ከሚያመጡት ወቅታዊ ውጤት በተሻገረ መልኩ ለመመልከት እንቸገራለን ። ቀድሞውኑም (እይታችን ከመጥበቡ የተነሣ) ጠባብ አድርገን የቀረጽነውን አጀንዳ በምንገልጽበት መንገድ የበለጠ እናጠብበዋለን ።
ነገር ግን ሁነቶችን እና ሒደቶችን ከመሠረታቸው መመርመራችን እና የምናቀርባቸው መፍትሔዎችም እንዲሁ የማይናወጥ መሠረት ያላቸው መሆናቸው አስፈላጊ ከሆነ ተዋሥኦውም እንዲሁ የጠለቀ እና የረቀቀ መሆን አለበት ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ፣ ማንበብ ፣ ማጠናቀር ፣ መወያየት ፣ መሟገት እና እንዲህ ካለው ሒደት የሚወጡትን ሐሳቦች የሚገባውን ጊዜ ወስዶ መጻፍ እና መናገር የግድ ነው ።
በተለይ የጽሑፎች አስፈላጊነት ደግሞ የተለየ ነው ። ጽሑፍ ከሌሎች ሐሳብን ማቅረቢያ አማራጮች ይልቅ ንጥር የሆኑ ሐሳቦች የሚገኙበት መንገድ ነው ። ጸሐፊው ሐሳቡን ለመግለጽ በአንድ ጊዜና ቦታ ሳይወሰን ፣ ደጋግሞ አስቦ ፣ ደጋግሞ ሞክሮ እስኪዋጣለት እና በበቂ መጠን ለማለት የፈለግሁትን ገልጫለሁ ብሎ እስኪያስብ ድረስ ሐሳቡን የሚያጠራበትን ዕድል የሚሰጥ ጎዳና ነው ። በመሆኑም መፍጠር ለምናልመው ተዋሥኦ ጽሑፍ የማይተካ ሚና አለው ። ያለ ጸሑፍ የሐሳቦች የማደግ አቅም የተወሰነ ነው ።
እንዲህ ያለውን ጽሑፋዊ ተዋሥኦ ለማድረግ ደግሞ እንዲህ ላሉ ጽሑፎች የተዘጋጀ መድረክ መኖር አለበት ። አሁን ያለው ከባቢ ግን ጽሑፍን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘነጋ እና እያገለለ ያለ ነው ። እንዲህ ያለው ጥልቅ እና ሰፊ ተዋሥኦ ቀርቶ ፥ ቀድሞ የነበረው ከወቅታዊ ጉዳዮች ያልዘለለ የጋዜጣ እና የመጽሔት ተዋሥኦ እንኳን ወደ መሞት ቀርቧል ።
ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወዳለው ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ ፥ እንዲህ ያለ ደንበኛ ተዋሥኦ ካለመኖሩም በላይ ፥ አሉ የሚባሉትም ምእመናንን ያገለሉ እና ዘመኑ ካመጣቸው ማዕበሎች ጨርሶ የተፋቱ ናቸው ። ራሳቸውን ካገኙበት ቦታ በግትርነት ወደፊት ከመግፋት ባሻገር ፥ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ላለማንሣት እና የቆሙበትን ቦታ ተገቢነት ላለመፈተሽ የቆረጡ ናቸው ።
በመሆኑም እንዲህ ያለው የጽሑፍ ተዋሥኦ የሚጠነሰስበት እና የሚዳብርበት ፣ ክርስትናን መሠረት ያደረገ መድረክ እንደሚያስፈልግ በማመን ፥ ኤማሁስ ፕሬስ ፥ ይህቺን ኤማሁስ የተሰኘች ፥ በጊዜያዊነት በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ፣ ወደፊት ግን በሕትመትም ጭምር ፥ በየሦስት ወሩ ለሕዝብ የምትደርስ መጽሔት ይዞ መጥቷል ።
፠ ፠ ፠
ኤማሁስ ‘መጽሔት’ ብትሰኝም ቅሉ ይዘቷ ለአካዳሚያዊ ጽሑፎች የሚቀርብ ይሆናል ። ከኤማሁስ ጀርባ ያለው ሐሳብ በትምህርቱ ዓለም (ቢያንስ በፊት) እንደሚደረገው ጥልቀት ያላቸው ጽሑፎችን ማስተናገድ ሲሆን ነገር ግን አሁን እየሆነ እንዳለው ከሕዝባዊው ተዋሥኦ ያልተነጠለ ፣ ይልቁንም በአንባቢነትም ሆነ በጸሐፊነት ለመሳተፍ ለሕዝቡ ክፍት የሆነ ተዋሥኦ መፍጠር ነው ። በመሆኑም ኤማሁስ ከተለመዱት መጽሔቶች በተለየ መልኩ ከሁነቶች ይልቅ መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ ያተኮሩ ፥ ወቅታዊ ጉዳዮችን ያማከሉ ነገር ግን ፍልስፍናዊ ይዘት እና ውቅር ያላቸውን ጽሑፎች ታስተናግዳለች ። የጸሐፊውን ስሜቶች እና አስተያየቶች መገለጻቸውን የምትወድ ፥ ነገር ግን ምክንያታዊነት ያልተለያቸው እንዲሁም የፍልስፍና እና የሐቅ መሠረት ላይ የቆሙ መሆናቸውን የምትጠይቅ ፥ ይህም መሆኑ እንዲታወቅ እንደ ትምህርታዊ ጽሑፎች በማጣቀሻዎች መደገፋቸውን የምታስገድድ ፣ ጠባብ በሆኑ የገጽ ብዛት ክልከላዎች ሐሳቦች እንዳይገደቡ ሰፊ ነፃነት የምትሰጥ መድረክ ትሆናለች ።
ከዚህ ይዘቷ እና ውቅሯ የተነሣም ወደ ሕዝብ ለመድረስ ሦስት ወር ያህል በዝግጅት ትቆያለች ። የሚነሡትን ሐሳቦች ስፋትና ጥልቀት ለማስተናገድ ስትል ሆዷን ታሰፋለች ፤ መለስ ያለ መጽሐፍ አክላ ትመጣለች ።
ለዚህ መድረክ የሚመጥኑ ጽሑፎችን ማዘጋጀት በእጅጉ አድካሚ ከመሆኑ የተነሣ ቢያንስ እስከ ጊዜው ድረስ የኤማሁስ አባላት በዋናነት የጸሐፊነት ሚናን መወጣት ቢኖርባቸውም ፣ ተስፋው ግን ከላይ እንደተባለው መድረኩ ሕዝባዊ እንዲሆን እና ብዙዎች በጸሐፊነት እንዲሳተፉ ነው ። ብዙ ሰዎችን ብቻም ሳይሆን ፥ ብዙ ዓይነት ሐሳቦችንም የሚያሳትፍ ተዋሥኦ መሆን አለበት ። የስምምነት እና የመደጋገፍ ብቻ ሳይሆን የሙግትም መድረክ ነው ለመፍጠር የምናልመው ።
ከአባቶቻችን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቷን እና ትውፊቷን የጠበቀችው እንዲህ ባለ ክርስቲያኖች እውነትን ፍለጋ በሚሟገቱበትም ተዋሥኦ ጭምር በመሆኑ እንዲህ ያለው ሙግት ለእኛ ዐዲስ ነገር ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የማስቀጠል ተግባር ነው ። ሌላው ቀርቶ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ያሉ ሰዎች እንኳን ሊሞግቱን ቢወዱ በቀናነት ለማስተናገድ በራችን ክፍት ይሆናል ። የክርስቲያኖች እምነት ባለማወቅ የሚጠበቅ ሳይሆን ተፈትኖ ያለፈ እና የጠራ መሆን አለበት ። አንድም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለነውን ከማጽናት ባለፈ ሌሎችን ወደዚህ ኅብረት መጥራትም የተልዕኮአችን ዋና አካል ስለሆነ ፥ የተዋሥኦውን አድማስ በተቻለ መጠን ማስፋት አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን ። ስለዚህም እንዲህ ያለውን ጥልቅ እና እውነትን መዳረሻው ያደረገ ተዋሥኦ የሚሹትን ሁሉ በማንበብም ፣ በመጻፍም ይሳተፉ ዘንድ እንጋብዛለን ።
እነኋት ኤማሁስ ።






ቃለሕይወት ያሰማልን
Looking forward to it.
Thanks so much for everything you have done
may God bless you and your pen too
እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባረክልን :በ podcast ብዙ እያተረፍን ነዉ በዚህ መምጣታችሁ ደግሞ የበለጠ እንድናተርፍ ይረዳናል እና በርቱልን
እግዚአብሔር የቅዱሳንን ጥበብ ያድልልን
“ጥሩ ነው በርቱ (ጥልቀት ያላቸው ሀይማኖታዊ ምርምሮችን ጨምራቸሁ ለአንባቢያን ክፍት ብታደርጉ) ።
ከዛሬ ጀምሮ የመጽሔቷ ደንበኝነቴን አረጋግጣለኹ ።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን 🙏
በርቱ ጊዜውን መዋጀት ያስፈልጋል።ይበል የሚያሰኝ ጅማሮ ነው።እንደ ቤተ ክርስቲያን ገና ብዙ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አሉብንና ወደፊት
በጣም አሪፍ ነው
እግዚአብሔር ያበርታቹ፣ የአገልግሎት ዘመናቹ ይባረክ:: ከወቅቱ ከሚመጣውም ጠላት እመብርሃን ትጠብቃቹ:: እንዲ ነው እንጂ ፣ የማንም ጥራዝ ነጠቅ ሁሉ $creen ሲያገኙ ጊዜ መርዝ ይተፋሉ:: በርቱልን:: ከጎናቹ ነን::
የአገልግሎት ዘመናችሁን ይባርክላችሁ🙏
ክፍት የሆነ የደጋፊንም የተቃዋሚን ሃሳብ ለመስማት የተዘጋጃቹ ልበ ሰፊ ስለሆናቹ ወደ ፊት ትልቅ ስራ እንደምትሄዱ እርግጠኛ ነኝ💪💪ጌታ በሁሉም ነገር ከናተ ጋር ይሁን🙏🙏
እጅግ ደሥ የሚል እይታ ነው። ሙግት የሚለው ትንሽ ከበድ የሚል ቢሆንም ሐይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እና ብዙም እንደምንማር ተሥፋ አደርጋለሁ። እንደቀደምት አበው የዘመኑ የቤተክርስቲያን ልጆቿም ብዙ ይተጋሉ፤ ለቀጣዩም ያስረክባሉ። ኮርቻለሁ፤ በርቱልን!!
ፈጣሪ አምላክ ይባርካችሁ!!
እግዚአብሔር ይስጥልን ጥቅምት ላይ እንገናኝ
አሪፍ ነው
እግዚአብሔር ይስጥልን!❤
በእውነት ድንቅ ነው!❤
ሙግት መኖር አለበት። ጤናማ ሙግት የሌለበት ተዋስኦ ሞዉት ነው። ይህ ዓይነት ባለመኖሩ የቀዘቀዘ፣የተደናበረ ምእመን ተፈጥሯል። በዚህም የተነሳ በቤት ውስጥ ይሁን በውጭ ያሉ እንዲጋልቡት ምቹ ሆኗል። የግላቸው መንጋ መሥራት ለሚፈልጉ ምቹ ገበያ ሆኗል።
ቃለህይወት ያሰማልን
አሪፍ ነዉ።
1.በርቱ ግን Meaninglessness በተመለከተ ያንሳል።Existentialism እና ቡዲዝም በደንብ ቢታይ ?
2.እንደሚታወቀዉ የቤተሰብ ዉቅር በየቤታችን እንዲፈረስ ተደረጓል ? ካለም በብዙ መለያየቶች ዉስጥ ነዉ “በሃይማኖት” ሳይቀር ይህ የሚያመጣዉ አደጋ በራሱ በጥልቀት ቢቀርብ? ከልጆች አስተዳደግ ጋር ሲያያዝ ደግሞ ሌላ ታሪክ ይህም ቢታይ?
3.እናዉጋ ላይ አማራነት አና ክርስትና እንኳን Boaring
ነበር።ለመሆኑ የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ከኛ Missionary mindset ደካማነት በተነሳ እንዳልከዉም የቅርስ እና ፉከራ ብዛት ዘረኝነት(ለዛዉም በደብር ሁላ)አኛንም እነሱንም እስካሁን ለWestern እና ለIslamic Captivity ተላልፈዉ እንዲሰጡት አላደረግንም ?
Orthodox is Missionary.ግን ነዉ እኛጋ?ለምን ?
4.”አበ ነፍስ” በክርስትና ሕይወት ዉስጥስ?
በርቱ !!!
ችግሩ የጋራ ነዉ ደሞ ።
ብሶቴን በአንዴ😂
መልካም መንገድ
እግዚያብሔር ከከፉ ይጠብቃችሁ።
ስለምትሰጡን እውቀት ሁሉ
እጅ ነስቻለሁ።
በተቻለኝ አዳምጣችኋለሁ።
ደሞም አነባለሁ።
በርቱ!!!